ኮሮና ቫይረስን የተመለከቱ መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ መቀበልና መከላከያ መልዕክቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ

 

ሀዋሳ፡ መጋቢት 08/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኮሮና ቫይረስን የተመለከቱ መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበልና መከላከያ መልዕክቶችን በመተግበር የተሳሳቱ መረጃዎችንና ፍርሀትን መከላከል እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገልጸዋል፡፡

 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እና ህብረተሰቡ ሊያደርገው ስለሚገባው ጥንቃቄ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

 

በመግለጫቸውም በክልሉ እሰከ አሁን ለቫይረሱ የተጋለጠ ሰው አለመገኘቱን ጠቁመው ነገር ግን ይህ ዋስትና ስለማይሆን ሳንዘናጋ የመከላከሉን ተግባር አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል፡፡

 

በክልሉ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሀይል ተቋቁሞ አስቀድሞ በሚሰሩ የመከላከል ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ቫይረሱ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ በክልሉ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እየታየ በመሆኑ በዚህ ተግባር በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል፡፡

 

ህብረተሰቡም ቫይረሱን በተመለከተ መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበልና መከላከያ መልዕክቶችን በመተግበር የተሳሳቱ መረጃዎችንና ፍርሀትን መከላከል እንደሚገባቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል፡፡

 

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው በክልሉ እስከ አሁን 39 የሚሆኑ በሽታው ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት የመጡ ተጓዦችንና ተጠርጣሪዎችን ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ በማድረግ የጤና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በቀጣይም የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረው ህብረተሰቡም የበሽታው ምልክቶች ሲያጋጥመው ለዚሁ በተዘጋጀው የነፃ ስልክ መስመር 6929 በመደወል መረጃ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

 

የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ሀዋሳ ከተማ በርካታ የውጪ ዜጎች የሚመጡበት ከተማ በመሆኑ ለችግሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የለይቶ ማቆያ ማዕከል በማዘጋጀት የተለያዩ የጥንቃቄና ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

መግለጫውን ተከትሎም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልልና የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በሀዋሳ ከተማ የሚገኘውን የለይቶ ማቆያ ማዕከልና ላብራቶሪ ጎብኝተዋል፡፡

 

ዘጋቢ፡ ኢያሱ ሽፈራው