በኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች አስፈላጊውን የመሬት አቅርቦትና ድጋፍ ይደረጋል - የደቡብ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው

ሀዋሳ፡ መጋቢት 09/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች አስፈላጊውን የመሬት አቅርቦትና ድጋፍ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ የክልሉ መንግስት ዝግጁ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ፡፡

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው ሁለተኛው ሃገር አቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንፍራንስ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ወርቁ አይተነው የተባሉ ባለሀብት በከተማው በቀን 1500 ቶን የምግብ ዘይት ሊያመርት የሚችል ፋብሪካና የጁስ ማቀነባበሪያ ለማቋቋም ቃል ገብተዋል፡፡

ባለሀብቱ በኮንፍረንሱ ስለ ሀዋሳ ከተማም ሆነ የደቡብ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለው ምቹ ሁኔታን በተመለከተ የተደረገው ገለፃ ለዚህ ውሳኔ እንዳበቃቸውም ገልፀዋል፡፡

ባለሀብቱ በከተማው ለመገንባት ቃል የገቧቸው ሁለቱ ፋብሪካዎች ተጨማሪ የስራ እድልን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ምስጋና ያቀረቡት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ትራቱ በየነ ለባለሀብቱ አስፈላጊውን ነገር በፍጥነት የማሟላት ስራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በባለሃብቱ ዘንድ የሚስተዋለው በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት የማድረግ ዝንባሌ ነገን በተሻለ እንድንጠብቅ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኮንፍራንሱ ባለሃብቱ በሀረሪ ክልል ተከስቶ በነበረ ችግር የገነቡት ሎጅ ለወደመባቸው አንዲት ባለሃብት የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍም አድርገዋል፡፡

የኮንፍራንሱ ተሳታፊ የነበሩት የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ የሀዋሳ ከተማን ከዛሬ 13 አመት በፊት እንደሚያውቋትና አሁን ላይ የደረሰችበት ደረጃ አስደናቂ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ወንድወሰን ሽመልስ