በደቡብ ክልል የጤና ኤክስቴንሽን ስራ መቀዛቀዙ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 09/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ክልል የጤና ኤክስቴንሽን ስራ መቀዛቀዙን የክልሉ ጤና ቢሮ የግማሽ አመት አፈፃጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበረዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ተገልጿል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበረዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቴ እንደገለፁት በክልሉ ጤና ቢሮ ወቅታዊ የጤና ጉዳዮችን ለመቅረፍ በቅንጅት በመስራቱ አድናቆት እንዳላቸው ገልፀው በቅርቡ በደቡብ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላክልና ለመቆጣጠር ከክልሉ የፊት አመራር ጋር በመቀናጀት የተሰሩትን ስራዎች በተሞክሮነት በመውሰድ በአሁኑ ጊዜ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላክልና ለመቆጣጠር የቅንጅት ስራውን በተመሳሳይ አጠናክሮ መስራት አንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ስራ መቀዛቀዝ ለጨቅላ ህፃናትና ለእናቶች ሞት ምክንያት እንደሆነ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸው ይህንም ለማስተካከል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት አንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የተጠሪ ተቋማት የኦዲት ሪፖርት በወቅቱ ያለማድረግ ችግር እንዳለ የተነሳ ሲሆን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛም ችግሩ መኖሩን ተናግረው ችግሩ የሚንፀባርቅባቸውም የጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና አንድ አንድ የጤና ተቋማት መሆናቸውንና በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል፡፡

ኃላፊ አያይዘውም የጤና ኤክስቴሽን ስራ የተቀዛቀዘ መሆኑን አንስተው ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው ሳይንሳዊ ጥናት የጤና ኤክስቴሽን ሰራ ወደነበረበት ሊመለስ የሚችል አንደሆነና በአሁኑ ጊዜም የፆታ ስብጥርን ባከተተ መልኩ ተቋሙ በመስራት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ