የደቡብ ክልል የብልፅግና ፓርቲ በክልሉ ለሚገኙ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና በስኬት መጠናቀቁ ተገለፀ

 

ሀዋሳ፡ መጋቢት 03/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ለአስራ አንድ ቀናት በክልሉ ለሚገኙ አመራሮች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና የተለያዩ ስኬቶች በማስመዝገብ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

 

የደቡብ ክልል የብልፀግና ፓርቲ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ሀላፊና የጽፈህት ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ አክሊሉ ታደሰ ስልጠናውን በማስመልከት ዛሬ በፓርቲው ፅህፈህት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

 

ለክልሉ አመራር የተሰጠው ስልጠና በአመራሩ የተግባርና የሀሳብ አንድነት መፍጠሩ የስልጠናው ዋና ስኬት መሆኑን ጠቅሰው በሀገራዊ ለውጥ የነበሩ ብዥታዎችን ማጥራት የተቻለበት ሰልጠና መሆኑን አብራርተዋል፡፡

 

በክልሉ የሚገኙ ከአስራ ሁለት ሺህ በለይ የሚሆኑ አመራሮች የተሳተፉበት ስልጠና ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ የተሰጠ መሆኑን ተናገረው ለሀገራዊ አንደነታችን መጎልበት ፓርቲው በትኩርት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በስልጠናው የፓርቲው የለውጥ ፍኖተ ካርታ ይፋ የተደረገ ሲሆን በፍኖተ ካርታው ላይ ተሳታፊዎች  ነፃ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

 

በስልጠናው በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በማህበራዊ ፖሊሲና በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ዙሪያ ለአመራሩ ግንዛቤ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

 

ጋዜጠኞች ላነሷቸው ጥያቄዎች አቶ አክሊሉ ታደስ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የህግ የበላይነትና ስርዓት ማስከበር ዋና ተግባር መሆኑን ገልፀው አመራሩ በሚመራው አካባቢ ህግን ማስከብር ካልቻለ አመራር ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ የጋራ ስምምንት መደረሱን አብራርተዋል፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለስልጠና ተሳፊዎች ዋና ዋና ጥያቄዎች ማብራሪያ መሰጠታቸው ስልጠናውን ልዩ የሚያደርገው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ