በደቡብ ክልል በሶስት ቀናት ውስጥ 11 የትራፊክ አደጋዎች ተከስተው በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

 

ከደረሱት 11 የትራፊክ አደጋዎች 7ቱ የሞት ሲሆኑ 3 ከባድ የአካል ጉዳትና 1 ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን በደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

 

ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከርና የአሽከርካሪው ጥንቃቄ ጉድለት የአደጋዎቹ መንስኤዎች መሆናቸውን ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት አክለዋል፡፡

 

በወላይታ ዞን ኪነዶ ዲዳይ ዘሮ ቀበሌ አካባቢ ህዝብ አሳፍሮ የነበረው አውቶብስ ለፍተሻ በቆመበት ቦታው ቁልቁለት መሆኑን ሳይገነዘብና ታኮ ሳያደርግ የወረዱት አሽከርካሪውና ረዳቱ አንዲት እንስት ዕቃ ረስቻለሁ በሚል ወደ መኪናው የገባች በመኖሯ መኪናው በራሱ ጊዜ ተንቀሳቅሶ ገደል ውስጥ በመግባቱ የእንስቷ ህይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡

 

በመሆኑም አሽከርካሪዎች ተሸከርካሪዎችን ሲያቆሙ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል ረዳት ኢንስፔክተሩ፡፡

ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ታደሰ