ድክመቶቻችን የጥንካሬዎቻችን ምንጮች በመሆናቸው ድክመቶቻችን ላይ አተኩረን መስራት አለብን ተባለ

ሀዋሳ፡ ጥር 14/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) ድክመቶቻችን የጥንካሬዎቻችን ምንጮች በመሆናቸው ድክመቶቻችን ላይ አተኩረን መስራት አለብን ሲሉ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ገነሞ ተናገሩ፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የቦንጋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ ሳልልህ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልዕክታቸውም ዘንድሮ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩ ቦንጋ ቅርንጫፍ መደረጉ ተቋሙ ያለበትን ሁኔታ በመገምገም የተጓደሉ ግብዓቶችን ለማሟላትና ልምድ ለመለዋወጥ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ገነሞ በበኩላቸው መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት በጎ አፈፃፀሞች እንደተጠበቁ ሆነው በአብዛኛው የምንገመግመው ድክመቶቻችንን በመሆኑና ድክመቶቻችን ደግሞ የጥንካሬዎቻችን ምንጮች በመሆናቸው በተለይ ባለፉት 100 ቀናት ባስቀመጥናቸው ግቦች ላይ ያተኮረ ውይይት መደረግ አለበት፡፡

መድረኩ በንግግር ከተከፈተ በኋላ የመድረኩ ተሳታፊዎች የቦንጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አጠቃላይ አሰራር ላይ ምልከታ አድርገዋል፡፡

በተያያዘም ተሳታፊዎች ኢትዮ አግሪ ሴፍት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር የሚገኘውን ውሽውሽ ሻይ ልማትን ጎብኝተዋል፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የዋናው ጣቢያና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የስራ ኃላፊዎች የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

በ100 ቀናት የአፈፃፀም ግምገማ መድረኩ የማዕከሉና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፡ ዳዊት ሺፈራው