በደቡብ ክልል የተጠየቁ የመዋቅር ጥያቄዎች የግጭት መንስኤ መሆን እንደማይገባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 08/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ክልል የተጠየቁ የመዋቅር ጥያቄዎች የግጭት መንስኤ መሆን እንደማይገባቸው የደቡብ ክልል ምሁራን በሆሳዕና ከተማ ባደረጉት የምክክር መድረክ ላይ ተገልጿል::

የደቡብ ክልልን በበላይነት በሚመራው ገዥ ፓርቲ ሰባት ወራት የወሰደው ጥናት ውጤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡት በዶክተር ካይሬዲን ተዘራ አማካይነት ለተወያዮች ቀርቧል::

የመዋቅር ጥያቄ ሁልንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈና በሰከነ ሁኔታ ለውይይት በማቅረብ ውሳኔ መስጠት እንደሚገ ተሳታፊዎች አንስተዋል::

እንደ ውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ይገባዋል፡፡ የአደረጃጀት ጥያቄ መፈጠር ዋናው ምክንያት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሲሆን በደቡብ ክልል ባለፉት ጊዜያት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወደ አንድ ማዕከል ያዘነበለ ነበር::

በተመሳሳይ መልኩ ሥነ ህዝብና ኢኮኖሚ ያላቸው ትስስር ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባዋል::

በደቡብ ክልል የሚኖሩ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የየራሳቸውን ባህላዊ የችግር መፍቻ መንገዶችን በመጠቀም አሉታዊ አተያዮችን ማስተካከል እንደሚገባቸው በውይይቱ ተነስቷል::

የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ከመመለሱ በፊት የፖለቲካ መረጋጋት መፈጠር መቻል አለበት ተብሏል፡፡

በማጠቃላይ ውይይቱ ላይ ሁሉም ለሀገራዊ አንድነት ሊቆም እንደሚገባ ዶክተር ካይሬዲን ተዘራ ገልጸዋል፡፡

በዶክተር ፋሪስ ደሊል አማካይነት ለክልሉ አመራር አስር ምክረ ሀሳብ ቀርቦ የውይይት መድረኩ መቋጫ ሆኗል::
ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ