የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ ከአባላትና ከደጋፊዎች ጋር  በሀዋሳ ከተማ ምክክር አደረገ

 

ሀዋሳ፡ ጥር 02/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ ከአባላትና ከደጋፊዎች ጋር በሀዋሳ ከተማ ሳውዝ ስታር ሆቴል ምክክር አድርጓል፡፡

 

በምክክር  መድረኩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ  መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ የፓርቲው አመራሮች ከአባላትና ደጋፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል::

 

በኢዜማ ፓርቲ ፕሮግራም፣ ቀጣይ የፓርቲው አሰራር፣ አባላት ምልመላን በተመለከተና የፓርቲው የኢኮኖሚ አማራጭ ፖሊሲ ላይ ከአባላትና ደጋፊዎች ጥያቄዎች ቀርበዋል::

 

በተያያዘም የብልጽግና ፓርቲ እና ኢዜማ ፓርቲ ተመሳሳይ ናቸው የሚል ሃሳብ ተነስቶ ማብራሪያ ተጠይቋል::

 

የኢዜማ ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከአባላትና ከደጋፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች  ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ በነፃነት እንዲኖርና እንዲንቀሳቀስ ኢዜማ የሚታገል መሆኑን ጠቅሰው ወጣቶች እውነተኛ ዲሞክራሲ በአገሪቷ እንዲገነባ መደማመጥ አሰፈላጊ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል::

 

አባላት ምልመላን በተመለከተ ከወረዳ ጀምሮ ፓርቲውን የማደራጀት ስራ በደቡብ ክልል መጠናቀቁን ገልፀዋል::

 

የኢኮኖሚ አማራጭ ፖሊሲን በተመለከተ ፖሊሲው የተዘጋጀ እንደሆነና ሙስና ከአገሪቱ ከጠፋ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማስተካከያ ዋና መንገድ እንደሆነ ተናግረዋል::

 

በአገራዊ አንድነት እና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ኢዜማና ብልጽግና ፓርቲ ተመሳሳይነት ያላቸው ቢሆኑም በፖሊሲ ላይ ፓርቲዎቹ ልዩነት እንዳላቸው ተናግረው ኢዜማ 43 የፖሊሲ አማራጮችን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል::

ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ