ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 21/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ የተገለጸው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና የጉራጌ ዞን ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ በወልቂጤ ከተማ ባዘጋጁት የምክክር መድረክ ላይ ነው::

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዞኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ደምስ ናቸው::

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ጾታዊ ጥቃቶች ባለፉት ጊዚያት መሻሻል ያሳዩ ቢሆንም ከሁለት ዓመት ወዲህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እያንሰራራ መሆኑን ኃላፊዋ ገልፀው የሀይማኖት አባቶች እና የህግ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲስሩ የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን አብራርተዋል::

የሴት ልጅ ግርዛት፣ እንጥል ማስቆረጥና ያለእድሜ ጋብቻ በዞን የሚታዩ ቢሆኑም የሴት ልጅ ግርዛት በተለያዩ ወረዳዎች በፍጥነት ማንሰራራት መጀመሩን ጠቁመው ይህን ለመከላከል በሰፊው ስራ መጀመሩን ተናግረዋል::

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት አቶ አስቻለው ዋሴ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ጥናት እንደተደረገና በዚህም የመንግስት ትኩረት ማነስ እንደሚስተዋል ጠቁመው በቀጣይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል::

በምክክር መድረኩ ከጉራጌ ዞንና ከወረዳዎች የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች፣ የፍትህ አካላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ