የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የበጎ ፍቃደኝነት ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ አዘጋጀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 16/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከታህሳስ 24 እስከ 30 የሚቆይ ዓለም አቀፍ የበጎ ፍቃደኝነት ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ማዘጋጀቱን ገለፀ፡፡

 

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታከለ ተሾመ መድረኩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የማህበሩ አባላትና የበጎ ፍቃደኞች ቁጥር መመናመን አስጊ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

 

ማህበሩ ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጋር የተያያዙ ተጨባጭ ስራዎችን እየሰራ ቢገኝም የግንዛቤ ፈጠራው ዝቅተኛ በመሆኑ የክልሉ ህዝብ ካለው የህዝብ ቁጥር አንፃር የተጠበቀውን አባል ማግኝት እንዳልተቻለ ገልፀዋል፡፡

 

ቀጣይ ቀናት የሚደረገው የህዝብ ንቅናቄ ይህን ለማሳካትና አገልግሎት አሰጣጡን ገጠር ድረስ ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ሀገር ያለ በጎ ፍቃደኛ ፈቀቅ የማለቷ ነገር አስቸጋሪ በመሆኑ ሁሉም የራሱን ኃላፊነት እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ባየ በልስቲ