የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ጋር ተወያዩ

ሀዋሳ፡ ህዳር 23/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ከሆኑት ኤልሲ ካንዛን ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በቀጣዩ ጥር ወር በዳቮስ ስዊዘርላንድ ከሚካሄደው 50ኛው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ጋር በተያያዘ እንዲሁም በሚቀጥለው ግንቦት ወር 2012 ዓም በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ''የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ምዕራፍ''በተመለከተም መረጃዎችን ተለዋውጠዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ፕሬዚዳንት ቦርጌ ብሬንዴ ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት በቀጣዩ ግንቦት ወር የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ምዕራፍ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ በመወሰኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም በዓለም ላይ ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ እና የሰው ልጆች ህይወት የተሻለ እንዲሆን እየተጫወተ ስላለው አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ፎረም በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ጋር በቅርበትና በትብብር እንደሚሰራ ገልጸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ገዱ አረጋግጠዋል።

ኤልሲ ካንዛን በበኩላቸው በጥር ወር 2012 ዓም በዳቮስ ስዊዘርላንድ የሚካሄደው ኢኮኖሚክ ፎረም ዓለም አቀፍ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ ተነሳሽነቶች ለሁሉም ባላድርሻ አካላት በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የፎረሙ አጀንዳዎችም በዋናነት የአየር ንብረት እና ከባቢ ለውጥ በዓለም ስነ ምህዳር እና ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሃሳቦች ፣ ኢንዱስትሪዎች በተለዋዋጭ የዓለም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሂደት ውስጥ የሸማቾችን መብትና ምርጫ ዘላቂነት ባላው መልኩ እንዴት ማስጠበቅ እንዳለባቸው የሚደረጉ ምክክሮች ናቸው፡፡
እንዲሁም ቴክኖሎጂ የጎንዮሽ ጉዳት ሳያስከትል ለህብረተሰቡ እና ለቢዝነስ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል፣ እንዲሁም የስነ ህዝብ፣ የማህበራዊ እና የቴክኖሎጅን አዝማሚዎች ከትምህርት፣ ከስራ እድል እና ከስራ ፈጠራ ክህሎት ጋር እንዴት ማጣጣም እንደሚቻል ምክክር እንደሚደረግ ኤልሲ ካንዛ አብራርተዋል።
በግንቦት ወር በኢትዮጵያ የሚካሄደው ''የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ምዕራፍ'' ጋር በተያያዘም ፎረሙ በአፍሪካ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን እና የግብርና ማቀነባበሪያን በማሳደግ አስተማማኝ የሰራ እድል መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚመክር ገልጸዋል።
ለዚህም ከወዲሁ አስፈገላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማከናወን አንደሚያስፈለግ ሚስ ኤልሲ ካንዛ ገልጸዋል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መቀመጫውን በዳቮስ ስዊዘርላንድ ያደረገ እና የዓለምን ሁኔታ ለማሻሻል የዓለም መሪዎች፣ ታዋቂ የቢዝነስ ካምፓኒ ሃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ባለሀብቶች የሚመክሩበት በ1963 ዓም የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ደርጅት እንድሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡