በጥራጥሬ ቅባትና ቅመማ ቅመም ላይ የሚስተዋሉ ሕጋዊ ያልሆኑ ግብይቶችን ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ህዳር 23/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጥራጥሬ ቅባትና ቅመማ ቅመም ላይ የሚስተዋሉ ሕጋዊ ያልሆኑ ግብይቶችን ለመቆጣጠር በትጋት እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኤፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ጋር በመተባበር ከህዳር 19 እስከ 20 በሸራተን አዲስ ሆቴል ባዘጋጀው ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና ቅባት ዕህሎች ኮንፍረንስ ላይ ነው፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርወቅ ገብረ እግዚአብሄር ኢትዮጵያ በዘርፉ ዕምቅ ሃብትና ተስማሚ የአየር ንብረት እንዳላት ጠቅሰው በተለይ በጥራጥሬ ቅባትና ቅመማቅመም ላይ የተሰማሩ አስመጪና ላኪ ድርጅቶችን በማቀራረብ፣ የንግድ ትስስርን፣ የውጭ ምንዛሬ አቅምን ለማሳደግና በዘርፉ የሚታዩ ሕጋዊ ያልሆኑ ግብይቶችን ለመቆጣጠር መንግስት ተግቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ሃይለ በርሄ በበኩላቸው የኮንፍረንሱን ዓላማ ሲገልጹ አገራቸው በዘርፉ ያለችበትን የእድገት ደረጃ ለሌላው ዓለም ለማሳወቅና ገጽታን ለመገንባት ሲሆን በዋናነት የሃገራችን ላኪዎች፣ ግብዓት አቅራቢዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና ዓለምአቀፍ የምርቶቻችን ገዢዎች በአንድ መድረክ በመገናኘት የቆየውን የንግድ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እና አዳዲስ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት መሆኑን ገልጸው በኮንፍረንሱ ላይ ከ20 የዓለማችን ሃገራት ባለሃብቶች እንደታደሙ አስታውቀዋል፡፡

በዕለቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርወቅ ገ/እግዚአብሄር ጨምሮ ከ350 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ምንጭ፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር