የአለም የኤድስ ቀን በሀዋሳ ታስቦ ዋለ

ሀዋሳ፡ ህዳር 23/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ክልል ደረጃ ትላንት የተጀመረው የአለም የኤድስ ቀን በዛሬው ዕለትም በሀዋሳ ከተማ ታስቦ ውሏል፡፡

በበአሉ ላይ የደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን ጋረደውን ጨምሮ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎችና የጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ አጋር ድርጅቶችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ስለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ግንዛቤው ባልዳበረበት ወቅት በክልሉ የፖለቲካ አመራሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የህክምና ባለሙያዎችና በዋናነትም ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች በተደራጀና በተናጠል በሰሩት አኩሪ ተግባር የተሻለ ውጤት መመዝገቡንና ተሞክሮም እንደተቀመረበት አስታውሰዋል፡፡

እንደ ከዚህ ቀደሙ ተከታታይ ስራ ባለመሰራቱና ለዚህ ስራ ከአጋሮችና ከሀገር ውስጥ የሚገኘው የበጀትና የቁሳቁስ ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ ችግሩን ለመግታት እንዳልተቻለ የገለፁት ዶክተር ጌታሁን አያይዘውም ዘንድሮ በዓሉን ስናከብር በ2030 ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለማስቆም የተያዘውን ግብ ለማሳካት ማህበረሰቡን ያሳተፈ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ዕለቱን አስመልክቶ ስለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አጠቃላይ መረጃ የያዘ ፅሁፍ በክልሉ ጤና ቢሮ የዘርፈ ብዙ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት ባለቤት በአቶ ሳሙኤል ዳርጌ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን አጋር ድርጅቶችም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ኢያሱ ሽፈራው