የሠላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ከከፋ ህዝብ ከተውጣጡ አካላት ጋር ውይይት አካሄዱ

ሀዋሳ፡ ህዳር 22/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሠላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ከከፋ ህዝብ የተውጣጡ አካላት ጋር ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄዱ፡፡

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ተሳታፊ የሆኑ የከፋ ህዝብ ተወካዮች እንዳሉት የካፋ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ በመሆኑ በመንግስት በኩል ተገቢው ምላሽ መሰጠት እንዳለበት አፅኖት ሰጥተዉ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ከከፋ ህዝብ ተወካዮች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት በመንግስት በኩል ህዝቡ ህገ-መንግስታዊ የሆነ ጥያቄዉን ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

አክለውም ራሳችንን ችለን በክልል እንደራጅ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሌሎች ዞኖችም መኖራቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ ቀጣይ ህዝቡን ያሳተፈ ውይይት እና ምክክር እያካሄደ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ ትላንት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከወላይታ ዞን ህዝብ የተውጣጡ አካላት ጋር ውይይት ማካሄዳቸዉ ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ