የደቡብ ክልል ምክር ቤት፣ የብሔረሰቦች፣ የዞን፣ የሀዋሳ ከተማ እና የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

 

ሀዋሳ፡ ህዳር 20/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) 17ኛው ዙር የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት፣ የብሔረሰቦች፣ የዞን፣ የሀዋሳ ከተማ እና የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ በደቡብ ኦሞ ዞን በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡


የተከበሩ ወ/ሮ ናኪያ አናቁስያ የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ለምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አሰተላልፈዋል፡፡

 

የደቡብ ኦሞ ዞን 16 ነባር ብሔረሰቦችና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች በመደመር የሚኖሩባት የፍቅርና የሰላም መንደር በመሆን እንደምትታወቅም ጨምረው ገልጸዋል፡፡


ክቡር አቶ ደርጌ ደሼ የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪም ውስን የሆነውን የመንግስትና የህዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ ከማዋል አንጻር ያሉ ጉድለቶችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች የተጠናከረ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡


አክለውም ዋና አስተዳዳሪው በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች ቋሚ የሆኑ ቋሚ ኮሚቴ እንዲኖር የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና የምክር ቤቶችን የክትትልና ቁጥጥር ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል አጋዥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡


የምክክር መድረኩን ያስጀመሩት የተከበሩ ወ/ሮ ሄለን ደበበ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥባቸው ምክር ቤቶች የተጀመሩ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ትልሞችን በማረጋገጥ የሀገራችን ህዝቦች አብሮ የመኖር የመቻቻል ባህል ለማስቀጠል ከቀድሞ በተሻለ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

 

የጋራ የምክክር መድረኩም የተመሰረተበት ዋና ዓላማም በምክር ቤቶች መካከል ያሉ ጉድለቶችን በማጥበብ በጋራ በመምከር የህዝቦችን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡


17ኛውን የጋራ ምክክር መድረክ ለየት የሚያደርገውም ሀገራችንን በግንባርነት ይመራ የነበረው ኢህአደግ ሀገርቱ የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ እና ለዚህም የሚመጥን ቁመና ላይ መሆን እንደሚገባ በማመን በግንባሩ ባሉ ድርጅቶች የጋራ ስምምነት ወደ አዲስ ምዕራፉ የብልጽግና ፓርቲ የሚሻጋገር መሆኑን ባሳወቅንበት ማግስት መደረጉ ነው ብለዋል፡፡


የምክር ቤቶች የ2ዐ11 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2ዐ12 ዓ.ም ዕቅድ በክልሉ ምክር ቤት የህግ ማውጣት ጥናትና ምክር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አማሩ ሀቱዬ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ምንጭ፡ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት