የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድና ተያያዥ አገልግሎቶች ክፍያ ተሻሽሎ ፀደቀ


ሀዋሳ፡ ህዳር 05/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ)የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድና ተያያዥ አገልግሎቶች ክፍያ በሚኒስትሮች ም/ ቤት ደንብ ቁጥር 450/2011መሰረት ተሻሽሎ ፀደቀ፡፡

 

በአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 1074/2010 መሰረት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለመስጠትና ተያያዥነት ላላቸው አገልግሎቶች የሚጠየቀው ክፍያ ማሻሻ ተደርጎበት በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 450/2111 ፀድቋል፡፡


በዚህ መሠረት ለአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ 680 ብር፣ ለብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ እድሳት፣ ምትክ ወይም ዓለም አቀፍ መንጃ ፍቃድ 620 ብር፣ ለማሰልጠኛ ተቋማት ወይም የራሳቸውን ሰራተኞች ለሚያሠለጥኑ ሌሎች ተቋማት አዲስ ወይም ምትክ ፈቃድ ደግሞ 5 ሺህ 175 ብር ሆኗል።

 

ከዚህ ባለፈም ለማሰልጠኛ ተቋማት ወይም የራሳቸውን ሰራተኞች ለሚያሠለጥኑ ሌሎች ተቋማት አዲስ ወይም ምትክ ፈቃድ ሲታደስ 2 ሺህ 570 ብር፣ ለቴክኒሽያን አዲስ ወይም ምትክ የብቃት ማረጋገጫ ወይም ጊዜያዊ የማሰልጠን ፈቃድ ደግሞ 435 ብር ይሆናል።

 

በተጨማሪም ለቴክኒሽያን ብቃት ማረጋገጫ ለማሳደስ ደግሞ 330 ብር መሆኑን ከፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።