ሕግን ማክበርና ማስከበር በጎ አመለካከት መኖር ለአንድ ማህበረሰብ ሰላማዊ ኑሮ አስፈላጊው ነው

ሰላም እና የሕግ የበላይነት በሁሉም ዜጋ ጥረት የሚገኝ ነው፡፡

 

ሰላም ከሰው ልጆች ወሳኝና መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ የሰላም ዋጋው እጅግ ውድ ነው፡፡ ያለ ሰላም እድገት፣ ብልፅግና ዴሞክራሲ የለም፡፡ በሰላም እጦት ዜጎችን ለድህነት፣ ለረሃብ፣ ለስቃይና ለጉስቁልና ይዳርጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ሰላም በሁሉም ዜጋ ጥረት የሚገኝ እንጂ የተወሰኑ ግለሰቦችና ተቋማት ርብርብ ብቻ የሚገኝ አይሆንም፡፡

 

ማማር፣ ማጌጥ ሁሉም በአገር እንዲባል፡፡ አገር የምታድገው፣ የምትበለጽገው፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲ ሲኖሩ እና በሕግ የበላይነት የሚገዛ ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡

 

ኢትዮጵያን የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት አገር ለማድረግ የተሻለ ሀሳብ ይዞ መሟገት እና በጋራ መሥራት ሲቻል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨት የአገራችን እሴት አይደለም፡፡

 

ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና ለዜጎች ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትህ በእኩልነት ተደራሽ እንዲሆን ተባብሮ መስራት ይገባል፡፡ አገር ፋይዳ ባለው የለውጥ ተግባር እንጂ በሥርዓት አልበኝነት አታተርፍም፡፡ ነፃነት፣ ፍትህና እኩልነት በተግባር ሊረጋገጡ የሚችሉት ሕጋዊነት የበላይ መሆን ሲቻል ነው፡፡

 

የሕግ የበላይነትን የማይቀበል በሰላም መኖር አይችልም፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ተቀዳሚ ኃላፊነት የአገርን ብሔራዊ ደህንነትና የሕዝቡን ሰላም ማረጋገጥ ቢሆንም መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር አለበት ሲባል፣ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ማረጋገጥ እንጂ ሕግ ይከበር ማለት መግደል ወይም በዘፈቀደ ማሰር ሳይሆን፣ ያጠፋው ማንም ይሁን ማን ሕግ ፊት ማቅረብ ማለት ነው፡፡ የሕግ መኖር የረጋና ሰላማዊ የሆነ ህብረተሰብ መፍጠር ነው፡፡

 

ውጤቱ እንዲያምርም ሕብረተሰቡ ስለሕግና ፍትህ ያለው አመለካከት ወሳኝነት አለው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ስለሕግና ፍትህ በጎ አመለካከት መኖሩ ለሕግ መከበር ቀዳሚ ሁኔታ ነው፡፡


አገር ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶች ቢኖሩም በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች ዜጎች መታመስ የለባቸውም፡፡

 

አገርን በጋራ ማሳደግ ግን የሁሉም አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ልዩነትን ይዞ የሕግ የበላይነትን በማክበር ለአገር በአንድነት መቆም የመልካም ዜጋ መገለጫ ነው፡፡ አገርን የሚያፈርሱ የጥፋት እጆችን መሰብሰብ እና ለአገር የማይበጁ ድርጊቶችን ማስወገድ ዘመኑ የሚጠይቀው የስልጣኔ መገለጫ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚናፍቀውን በሰላም፣ በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚኖርበት ሥርዓት ለመገንባት ነው፡፡ ሕግን ማክበርና ማስከበር በጎ አመለካከት መኖር ለአንድ ማህበረሰብ ሰላማዊ ኑሮ አስፈላጊው ነው፡፡

 

የአገር ፍቅር ትርጉሙ ለአገር ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት በመክፈል መታደግ እና ዘለቄታዊ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚገኘው በመነጋገርና ለጋራ አላማ ስኬት መደመር ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰላማዊትና የዴሞክራሲዊት አገር እንድትሆን ከተፈለገ ለሕግ የበላይነት መገዛት የግድ ነው፡፡

 

በአንድ አገር ሰላምና መረጋጋት የሚኖረው ሕዝብ በነፃነት መኖር ሲረጋገጥ ነው፡፡ ፍትህ የእኩልነት ማረጋገጫ፣ ፍትህ የምክንያታዊነትና የእውነት ማንፀባረቂያ ሲሆን ፍትህ በሌለበት ክብር የለም እና የሕግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መልካም ልብ፣ መልካም አስተሳሰብ ማዳበር በሕግ የበላይነት መገዛት አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው፡፡ ሰላምና ብልፅግና ለአገራችን ይሁን!

ምንጭ፡ የኢፌድሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ