ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የዩናይትድ ስቴትስ አፍሪካ እዝ አዣዥ ከሆኑት ከጀነራል ስቴፈን ታውንሴንድ ጋር ተወያዩ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 26/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የዩናይትድ ስቴትስ አፍሪካ እዝ አዣዥ ከሆኑት ከጀነራል ስቴፈን ታውንሴንድ ጋር መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በውይይታቸው ወቅት ጀነራሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በቅርቡ ባገኙት የኖቤል ሰላም ሽልማት ደስታቸውን ገልጸው ይህ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው አበረታች ድል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ቀጥሎም በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል በተለይም ከወታደራዊ የጦር ኃይል አንፃር የነበረውን የረዥም ጊዜ የትብብር ግንኙነት በማስታወስ፣ የሀገሪቱን ጦር ሠራዊት አቅም ለመገንባት የአጭር እና የረዥም ጊዜ ትብብርን በማጠናከር ላይ ተወያይተዋል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ እየተከናወነ የሚገኘውን የተሀድሶ ሥራ ከማስቀጠል አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ሠራዊቱን ብቃት ያለው ባለሙያ ማድረግ እና ለየትኛውም አካል እና የፖለቲካ ተቋም ምንም ዓይነት አድልዎ ሳያሳይ ወገናዊነቱን ለዲሞክራሲ ብቻ ያደረገ እንዲሆን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት