የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለፀ፡፡

ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ በአገራችን የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ተመራማሪ በመሆን ህዝባቸውን እና አገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ ታላቅ ባለውለታ ናቸው፡፡

ዶ/ር ቦጋለች፤ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል ካከናወኑት መልካም ተግባር በተጓዳኝ በአካባቢ ጥበቃ እና በአረንጓዴ ልማት መስክ ዘመን ተሻጋሪ አሻራዎች አኑረዋል፡፡

የእናቶችን እና ሕፃናትን ሞት ለማስቀረት ያበረከቱት ዘርፈ ብዙ ተግባር ለክልላችን ብሎም ለሀገራችን ሴቶች በአርአያነት የሚጠቀስና ስራቸው ከመቃብር በላይ ሲታወስ ይኖራል፡፡

ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ባበረከቱት መልካም ተግባር በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶችን የተሸለሙና ጠንካራ ባለብሩህ አዕምሮ እንስት ናቸው፡፡

ዶክተር ቦጋለች ገብሬ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለአድናቂዎቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡
የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት