ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረገውን የሦስቱ ሀገራት ውይይት እደግፋለሁ አሉ

 

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን የሀሳብ ልዩነት በውይይት ለመፍታት የጀመሩትን ሥራ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

 

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት ዛሬ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት መሆኑን ዋይት ሀውስ ጠቅሷል።

 

አል ሲሲ ሦስቱ ሀገራት በውይይት ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንዲፈጥሩ ለሚያደርጉት ድጋፍ ትራምፕን ማመስገናቸውን አል ጀዚራ በዘገባው አትቷል።

 

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በአሜሪካ ጋባዥነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለመወያየት ወደ ዋሽንግተን አቅንተዋል።

 

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ትናንት ወደ ዋሺንግተን ዲሲ መጓዛቸውን ቃል አቀባዩ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

 

ነገ በሚካሄደው ውይይትም አሜሪካ ሶስቱ ሀገራት በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አቋም ለመስማት የጠራችው እንደሆነ ገልጸዋል።

 

በግብጽ መገናኛ ብዙሃን “ድርድር ነው እየቀረበ ያለው በሚል የሚቀርበው ዘገባ ስህተት” እንደሆነ ጠቅሰው የዋሺንግተን ዲሲው ውይይት ሀገራቱ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አቋም የሚገልጹበት ነው ብለዋል።

 

የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴቨን ሙንቺን ጥሪ ያደረጉት ለሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብቻ እንደሆነና የቴክኒክ ጉዳዮች የውይይቱ አጀንዳ እንዳልሆነም አመልክተዋል።

 

ኢትዮጵያም በውይይቱ ላይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም እንደምታቀርብና የተቋረጠው የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲቀጥል በተደጋጋሚ እያንጸባረቀች ያለውን አቋሟንም ለአሜሪካ ትገልጻለች ብለዋል።

 

የዋሺንግተን ዲሲው ውይይት ኢትዮጵያ ለአሜሪካ በግድቡ ዙሪያ ያላትን አቋም ለማስረዳት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም ነው አቶ ነቢያት ያስረዱት።

 

“አሜሪካ የህዳሴ ግድቡ ጉዳዮች በቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ ምላሽ እንዲያገኙ ብታበረታታ የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው” ሲሉም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።