ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በይፋ ተጀመረ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 24/2012 (ደሬቴድ) በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዘጋጅነት “ትኩረት ለሳይበር ደህንነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በይፋ ተጀመረ፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤፍራህ አሊ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንትን የማክበር ዓላማ በዘርፉ ያለው ንቃተ-ህሊና ዝቅተኛ በመሆኑ የህብረተሰቡንና የተቋማትን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በሀገራችን ከዓመት አመት እየደረሱ ያሉ የሳይበር ጥቃቶች በየጊዜው እያደጉ መምጣታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከምንግዜውም በበለጠ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የሰላም ሚንስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው “ትኩረት ለሳይበር ደህንነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የሳይበር ደህንነት ሳምንት ወቅቱን የጠበቀ እና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

ዓለም በሳይበር ምህዳር አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን የሳይበር ኃይል ከገንዘብ፣ ከጦር መሳሪያ እና መሰል አቅሞች በላይ የሆነ የዘመናችን ቁልፍ መወዳደሪያ አቅም መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዘይኑ ጀማል ገልፀዋል፡፡

ሚንስትር ዴኤታው የሳይበር ደህንነት ለሃገራችን አዲስ እና በርካታ የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈልግ እንደመሆኑ መጠን በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ሃይል አቅም በመገንባት እና አዲስ የሰው ሃይል በማልማት አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ ግብዓት በማሟላት ሊመጣብን ከሚችል ማናቸውም ጥቃት ራሳችንን መጠበቅ እንችል ዘንድ መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

የህረተሰቡን አስተሳሰብ በመቀየር ረገድ የመሪነት ሚናን የሚጫወቱት የመገናኛ ብዙሃን የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት የፕሮግራሞቻቸው አንድ አካል አድርገው በመቅረጽ ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ዘይኑ ጀማል ገልጸዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታው ኤጀንሲው ያዘጋጀውን ትኩረት ለሳይበር ደህንነት ሳምንተ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተቋማት የአመራሮች እና ሰራተኞችን እንዲሁም የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ለማሳደግ የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በዓለም ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ እንደሚገኝ ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡