በኩታ ገጠም የተመረተ የቢራ ገብስ በከፍተኛ አመራሮች ተጎበኘ

በሲዳማ ዞን ማልጋ ወረዳ በኩታ ገጠም የተመረተ የቢራ ገብስ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል፡፡

በሲዳማ ዞን ማልጋ ወረዳ በክልሉ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም እና በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ካስኬፕ ፕሮግራም ድጋፍ የለማን የቢራ ገብስ ማሳን ነው በክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ የተካሄደው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የብቅል ወይም የቢራ ገብስ የኢንዱስትሪ ሰብል በመሆኑ ለአምራች አርሶ አደሮች የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አገራችን የቢራ ገብስን ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ በማውጣት መሆኑን ጠቁመው የማልጋ ወረዳ አርሶ አደሮች የጀመሩትን መልካም ተሞክሮዎች ወደ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በማስፋት ከውጪ አገር የሚገባውን በአገር ውስጥ በማምረት መተካት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በቀጣይ ቢሮው የክልሉ አርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኙ የሰብል አይነቶችን እንዲያመርቱ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በወረዳው በመኸር እርሻ ከለማው 3 ሺህ 458 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ 2 ሺህ 546 በላይ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ የለማ ነው፡፡

ክልሉ የቢራ ገብስን በስፋት ለማልማት የሚያስችል ምቹ የሆነ ዕምቅ ፀጋ መጎናፀፉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የብቅል ወይም የቢራ ገብስ በክልሉ ከሚመረቱት የኢንዱስትሪ ሰብሎች መካከል አንዱ ሲሆን በሁለተኛ ምዕራፍ የግብርና ሴክተር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የድርጊት መርሃ ግብር ዓመታት ዘርፉን ለማዘመን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡