በአፍሪካ ቀንድ የታየው መልካም የትብብር መንፈስ በመላው አፍሪካ ሊሰፋ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአፍሪካ ቀንድ የታየው መልካም የትብብር መንፈስ በመላው አፍሪካ ሊሰፋ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

አፍሪካውያን ድህነትን ከመዋጋት ወደ ብልጽግና መገንባት ይበልጥ በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሩሲያ አፍሪካ የትብብር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ኢትዮጵያ 'መደመር' በሚል እሳቤ ያልተጠቀመቻቸውን አቅሞች በማሰባሰብና ስህተቶችን በማረም ብሩህ አገር ለመገንባት እየሰራች መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህም ከአገር ውስጥ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ መልካም ትብብር እንዲፈጠር ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የታየው ትብበር ወደ አህጉራዊ ትስስር መስፋት እንዳለበትም ተናግረዋል።

አፍሪካውያን በስፋት ሊተሳሳሩባቸው የሚችሉ እንደ ማዕድንና ግብርና የመሳሳሉ እምቅ አቅሞች አሏቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችሉ ትብብሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለም የተጋረጠባትን ውስብስብ ችግር መፍታት የሚቻለው መተባበር ሲኖር ብቻ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጠዋል።

የሩሲያ አፍሪካ የትብብር መድረክ ከዚህ አንጻር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል። (ኢዜአ)