ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የላቀ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ እና የደቡብ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ከአቶ እርስቱ ይርዳ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በተወያዩበት ወቅት ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የላቀ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ እና የደቡብ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስራ አስፈጻሚ አባላት ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ከአቶ እርስቱ ይርዳ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያደረጉትን ውይይት በጸሎት የከፈቱ ሲሆን በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የደቡብ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስራ አስፈጻሚ አባላት በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ዛሬ በጋራ ያደረጉት ውይይት በ3 አበይት አጀንዳዎች ላይ መክሯል፡፡

በክልሉ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ እያካሔደ ያላቸው ስራዎች ዝርዝር አፈጻጸም፤ በሲዳማ ዞን ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን የሀይማኖት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እና ከዞን ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አደረጃጀትና አሰራር ላይ መምከር የውይይቱ አበይት ጉዳዮች ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደሰ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት ከደቡብ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማገዝ ያደረገው ጥረት ስኬታማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ገለጻ ቀደም ሲል በሲዳማ ዞን ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር የተጎዱ የሀይማኖት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሀይማኖት አባቶችን በማነጋገር እና ኮሚቴ በማዋቀር ተቋማቱን መልሶ ለማደራጀት ያደረጉት ጥረት አበረታች ነው ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንድ አንድ ዞኖች የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያለውን ፋይዳ በተገቢው ሁኔታ ካለመረዳት የተነሳ አደረጃቱን ከመፍጠር ጀምሮ በጋራ ተቀናጅቶ ከመስራት አንጻር ጉድለቶች መታየታቸውን አውስተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሁሉንም የሀይማኖት አባቶች ማክበር መደማመጥ እና መመካከር ለአንድ መሪ አባይት ተግባራት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ገለጻ ያለንበት ዘመን ቴክኖሎጂው ያደገበት እና ሉላዊነት የተስፋፋበት ጊዜ በመሆኑ የሐይማኖት አባቶች አስተምህሮት እና ተግሳጽ ትውልድን በስነ-ምግባር ለማነጽ ያለው ሚና የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ እውቅና ያለው እና የተደራጀ ተቋም በመሆኑ ከዚህ ተቋም ጋር ተባብሮ በመስራት ጊዜና ሀብትን በተገቢው ሁኔታ ለመምራት የሚያግዝ በመሆኑ በጋራ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉን ለመደገፍም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚሰራው ስራ ለማገዝ ከክልል እስከ ወረዳ ያለውን መዋቅር እንዲጠናከር በማድረግና በየሩብ አመቱ የስራ እንቅስቃሴውን በጋራ እየተገመገመ የሚመራ እንደሚሆን የዘገበው የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው፡፡