የደቡብ ክልል መንግስት የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በአራት ተቃውሞ በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጸደቀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 06/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በአራት ተቃውሞ በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል፡፡

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድ ያቀረቡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች በምክትል ርዕስ መስተዳድሩና ዘርፉን በሚመሩ የቢሮ ኃላፊዎች ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ቀደም ሲል በክልሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የበጀት ዕጥረት መኖሩን ገልጸው በያዝነው በጀት ዓመት አዲስ ፕሮጀክት እንደማይኖርና የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረውዋል፡፡

ለሰራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ለተጀመሩ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ግንባታ ሀብት በማፈላለግ ይሰራል፡፡ ለሰራ ዕድል ፈጠራ ቁጠባን የሀብት ምንጭ በማደረግ መሰራት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

በትምህርቱ ዘርፉ የመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና አዳዲስ የመምህራን ቅጥር መፈጸም እንደሚገባው ተናግረናል፡፡

በገቢ አሰባሰብ ረገድ ክፍተት እንዳለና ከ6 ቢሊየን ብር ባላይ በክልል ደረጃ ገቢ አንዳልተሰበሰበ በሪፖርቱ አመላክተው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት ካልተቻለ የሚጠበቀውን ልማት ማምጣት እንደማይቻል አብራርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በበጀት ዕጥረት ምክንያት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደማይደረግ ገልጸው ህብረተሰቡን በየአካባቢው በሚደረጉ አነስተኛ የመንገድ ስራዎች ላይ ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የተለያዩ ዘርፎችን የሚመሩ የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት የ2012 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ቀርቦ በምክር ቤቱ አባላት አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል፡፡

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባዔ እስከ ጥቅምት 7/2012 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል፡፡
ዘጋቢ፡ ፋሲል ኃይሉ