በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

ሀዋሳ፡ መስከረም 16/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ74ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።


ፕሬዚዳንቷ በአማርኛ ባደረጉት ንግግራቸው በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት በበርካታ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት በማስከበር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተሳትፎና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር በርካታ ስራዎች እያከናወነች መሆኗንም አክለዋል።
በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ስራ የሀገር ተጠቃሚነትን ባረጋገጥ መልኩ ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር በመቅረፅ አበረታቸ ስራ መስራቷን ነው የተናገሩት።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያለውን የፀጥታና የደህንነት ሁኔታ ከማስከበር አንፃርም ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣች የምትገኝ መሆኑን አውስተዋል።
እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ የአባይ ወንዝ በተመለከተ ባደረጉት ንግግርም ወንዙ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የጥርጣሬ እና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም ነው ያሉት።
የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀምም የተፋሰሱ ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ቋሚ መቀመጫ አንዲኖራት ጠይቀዋል።