ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ አማራጭ ምልክቶችን ይፋ አደረገ

ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2012 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ የሚካሄድባቸውን አማራጭ ምልክቶች ይፋ አደረገ።

ቦርዱ ሕዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሲዳማን ዞን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ ለማካሄድ ላቀደው ሕዝበ ውሳኔ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

ሁለቱ የህዝበ ውሳኔ አማራጭ ሃሳቦች የሚወከሉበትን ምልክቶች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልና ከሲዳማ ዞን ምክር ቤት ጋር በመምከር ሁለት አማራጭ ምልክቶችን ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት ”ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ እንዲቆይ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የጎጆ ቤት ምልክት እንዲሆን ወስኗል።
እንዲሁም ”ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ለሚለው አማራጭ የሻፌታ ምልክት ሆኖ ለህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫነት እንዲያገለግል የተወሰነ መሆኑን ቦርዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል። (ኢዜአ)