የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
 
የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲሱ ዓመት የጤና፣ የሰላም፣ የብልጽግና እና የአገሪቷን አንድነት በማጠናከር እንደ ሐገር በስኬት የምንረማመድበት እንዲሆን ተመኝተዋል።
 
 
ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላኛው የሚደረገው ሽግግር ቀን ቀጥሮ አሮጌውን ከመሸኘት እና አዲሱን ዓመት ከመቀበል ያለፈ አንድምታ አለው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ አዲሱ ዓመት ተስፋን ሰንቀን ወደ ተሻለ ህይወት ራሳችንን የምናዘጋጅበት እና ወደፊት አሻግረን ለምናየው ህልማችን የብርሃን ወጋገን የሚሰጥልን የጥንካሬያችን ምንጭ ሲሉ ገልጸውታል።
 
በአሮጌው ዓመት ችግሮች እንዳሉ ሆኖ በብዙ መለኪያዎች የተለየ ዓመት እንደነበር ያወሱት ፕሬዝዳንቷ፤ ዜጋው በሃገሩ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆን መንገዱን የሚጠርጉ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች መሰረት የጣሉ ስራዎችም የተከናወኑበት ዓመት ነበር ብለዋል።
 
ዓመቱ በአገሪቷ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ በር የተከፈተበት መሆኑን በመግለጽ፤ ከጥቂት ወራት በፊት ማንም በማያስበው ሁኔታ ለሴቶች የይቻላል መንፈስን የፈጠሩ ሁኔታዎች የተከሰቱበት እንደነበርም በማሳያ ጠቅሰዋል።
 
በአመለካከታቸው የተነሳ ተራርቀው የነበሩ ወገኖች በአገር ጉዳይ ላይ በጠረንጼዛ ዙሪያ ለመቀመጥና ለመወያየት መብቃታቸው በማውሳት፤ በአመለካከት እና በእምነት መለያያት ቢኖርም የጋራ ጉዳያችንን መሳት አይገባውም በማለት፤ የሚያስተሳስረን ገመድ ኢትዮጵያዊነት ነው ብለዋል።
 
በአገራችን ሁኔታ ሊያስተሳስረንና ሊያግባባን የሚገባው ጉዳይ ወገኖቻችንን ከድህነት ማላቀቅ፣ መሰረታዊ ፍላጎቶታቸውንና መብቶቻቸውን ማስከበር ሊሆን እንደሚገባውም ጠቅሰዋል።
 
አገሪቷ የተያያዘችው የለውጥ ሂደት ካለፉት ብዙ የተለየ የሚያደርገው የነበረውን ጠራርጎ "ሀ" ብሎ የጀመረ ሳይሆን ለአገሪቷ እድገትና ብልጽግና እሰለፋለሁ የሚለውን ሁሉ አስተባብሮ ለመጓዝ የተነሳ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህ ደግሞ የራሱ የሆኑ አዳዲስ መሰናክሎች ያመጣ መሆኑን ከመግለጽ አልተቆጠቡም።
 
በተለይም ባለፉት ጊዜያት ያየናቸው አስከፊ ሁኔታዎች በሀገሪቷ እንዳይከሰቱ የማድረግ ሃላፊነት የመንግስት ወይንም የተወሰኑ አካላት ላይ ብቻ የሚጣሉ አይደሉም ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ የአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የልማት ጉዳይ ለይደር የሚተው አለመሆኑን ገልጸዋል።
 
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለግል ወይም ለቡድን ፍላጎት ብቻ ብሎ ለአንድ ወቅት የፖለቲካ ጥቅም የሚደረጉ ቀይ መስመር ያለፉ ተግባራት በስተመጨረሻ ልንመልሰው ወደማንችለው መቀመቅ እንዳይከተን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ቀጣዩ አዲስ ዓመት አገርን በጽኑ መሰረት ላይ የምናስቀምጥበት፤ ተቋሞቻችንንና ተቋማዊ አሰራሮቻችንን፤ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ምዕራፍ እናድርግ በማለት መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
 
አባቶቻችንና እናቶቻችን ያስተማሩን በችግሮቻችን ተውጠን ከስመን መቅረትን ሳይሆን ከችግሮች መካከልም የማይደበዝዙ ድንቅ ተግባራት በመፈጸም በሁለት እግር መቆም እንደምንችልም ጭምር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ በመጪው ዓመት ሰላሟና ደህንነቷ የተረጋገጠ አገር እንደሚፈጠር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።