የኢንተርኔት ግንኙነት ባላቸዉ ቁሳቁሶች ሳቢያ ከሚደርስ የሳይበር ደህንነት ስጋት ራሳችንን እንጠብቅ ተባለ፡፡

ሀዋሳ፡ ጷጉሜ 06/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢንተርኔት ግንኙነት ባላቸዉ ቁሳቁሶች ሳቢያ ከሚደርስ የሳይበር ደህንነት ስጋት እንዴት ራሳችንን መጠብቅ እንዳለብን የኢንፎርሜሽን መገናኛና ደህንነት ኤጀንሲ መረጃ አውጥቷል፡፡

አዲስ አመት ዋዜማ ላይ እንደመሆናችን ብዙዎች ከዘመድ አዝማድ ጋር አውዳመቱን ለማሳለፍ በየአቅጣጫው ይጓዛሉ፡፡ ታድያ በዚህ ጉዞ ወቅት ሁሌም ከእጃችን የማይለየን አንድ ነገር ቢኖር ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን እና ሌሎች እንደ ላፕቶፕና ታብሌት የመሳሰሉ የኢንተርኔት መጠቀምያ ቁሳቁሶች ናቸዉ፡፡

ለመሆኑ በእነዚህ ቁሳቁሶች ሳቢያ እንዴት ለሳይበር ጥቃት ልንጋለጥ እንችላለን እንዴትስ ራሳችንን ከጥቃት መጠበቅ እንችላለን?
ተንቀሳቃሽ ቁሳቁሶች ከቦታ ቦታ ይዘን በምንቀሳቀስበት ወቅት መውሰድ ያለብን ጥንቃቄ፡-
• ነፃ ፐብሊክ ዋይፋይ ኔትዎርኮችን በየቦታው አለመጠቀም፡- ከቦታ ቦታ በምንቀሳቀስበት ወቅት ባለቤቱ የማይታወቅና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ የዋይፋይ አገልግሎትን መጠቀም በተለይም ሚስጥራዊ መሆን የሚገባቸዉን የኦንላይን ተግባራት መፈፀም ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል፤ በመሆኑም የዋይፋይ አጠቃቀማችን ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል፡፡
• የብሉቱዝ ግንኙነትን ወዲያው ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር ክፍት አለማድረግ፡- ይህም ጥቃት አድራሾች የብሉቱዝ ግንኙነትን በመፍጠር ጥቃት ማድረስ ሥለሚችሉ የብሉቱዝ አገልግሎት በማንፈልግበት ጊዜ ብሉቱዛችንን ማጥፋት ይኖርብናል፡፡
• የኢንተርኔት መገልገያዎችን ቻርጅ ስናደርግ ጥንቃቄ ማድረግ፡- የኢንተርኔት መገልገያዎቻችንን ቻርጅ በምናደርግበት ወቅት በኬብሎች አማካኝነት ከኮምፒዉተሮች ጋር ስናገናኝ ለአደጋ ተጋላጭ ስለምንሆን እና ማሊሺየስ የሆነ ሶፍትዌርም የሚተላለፍበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል የምናውቀው ኮምፒውተር ላይ ብቻ በጥንቃቄ ቻርጅ ማድረግ ይኖርብናል፡፡
• አካዉንቶቻችን ወይም መረጃዎቻችን እንደተጠለፉ ወይም አላግባብ ጥቅም ላይ እንደዋሉ ካወቅን ደግሞ ለተገቢዉ አካል ማመልከት እና እርዳታ መጠየቅ ተገቢ ነዉ፡፡ ለምሳሌ አለም አቀፍ ጉዞዎችን ያደረግን ከሆነ በምንገኝበት ቦታ የደህንነት አካላት ሪፖርት ማድረግ ተገቢ ነዉ፤
ምንጭ፡ የኢንፎርሜሽን መገናኛና ደህንነት ኤጀንሲ