በዓልን አስመልክቶ በእንስሳት እርድ ወቅት መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎችን በተመለከተ የፕሬስ መግለጫ ተሰጠ፡፡

ሀዋሳ፡ ጷጉሜ 06/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) አብዛኛዎቹ ሰውን የሚያጠቁ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው፡፡

ከመተላለፊያ መንገዶቹም ዋነኛው ከእንስሳት እና የእንስሳት ተዋፅዎችን በመመገብ ሲሆን ጥሬ ስጋ ዋነኛው የመተላለፊያ መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም እነኚህንም በሽታዎች እንዲሁም የጥሬ ቆዳና ሌጦ ብክነትንና የጥራት ጉድለትን ለመከላከል ሁሉም ህብረተሰብ የሚከተሉትን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

1. ለእርድ የሚሆኑ እንስሳትን ስንመርጥ በተቻለ መጠን ምንም አይነት የበሽታ ምልክት የማያሳዪ፣ ደካማ ያልሆኑ፣ ትክክለኛ አቋም ያላቸው፣ ከሰውነት ቀዳዳዎቻቸው ፍሳሽ የማያሳዩና በጣም ያልከሱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
2. የእርድ እንስሳት በመኪና ሲጓጓዙ እንስሳቱን አለመደብደብ እና በመኪናው ላይ በቂ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ እንስሳቱን አለማሯሯጥ፣ እረፍት እንዲያገኙ ማድረግ፣
3. እንስሳት በቄራዎች ማሳረድ ይመከራል፡፡ ምክንያቱም በእንስሳት ጤና ሙያ እና በስጋ ምርመራ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንስሳት ከመታረዱ በፊትና ከታረደ በኋላ ምርመራ በማድረግ ስጋው ለሰው ምግብነት መዋል አለመዋሉን ያረጋግጣሉ፡፡ ለሰው ምግብነት መዋል የማይችለውን እንስሳት/ክፍል በማስወገድና ለሰው ምግብ የሚውለውን በማህተም በማረጋገጥ ለተጠቃሚ ማድረስ ይቻላል፡፡
እንስሳትን በቤት ውስጥ ማረድ ባይመከርም በቤት ውስጥ የምናርድ ከሆነ
1. ከየወረዳችን የእንስሳት ጤና ባለሙያ በመጥራት የቅድመ-ዕርድና ድህረ-ዕርድ ምርመራ እንዲያደርግልን ማድረግ፣
2. እንስሳትን የምናርድበት ቦታና መገልገያ መሳሪያ ከቆሻሻ የፀዳ መሆኑን ማረጋገጥና
3. በእርድ ሰአት ብዙ ውሃ በመጠቀም ከቆሻሻ ጋር ንክኪ ያለው የስጋ ክፍል ካለ በአግባቡ ማጠብ ወይንም ቆርጦ ማስወገድ
4. እራስን ለመከላከል የምንጠቀምባቸው እንደ ፀጉር መሸፈኛ፣ የእርድ ልብስ እና ጫማ ንፅህናቸውን የጠበቁ መሆን እና
5. የማረጃ ቢላዋ፣ የመሰንዘሪያ እና የመግፈፊያ ቢላዋዎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በማድረግ የምንበላውን ስጋ ጤንነት ማረጋገጥ ከመቻላችንም ባሻገር ከእንስሳት ወደሰው ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን መከላከል እንችላልን በተጨማሪም ጥሬ ቆዳና ሌጦ በአጭር ጊዜ ለብልሽት ስለሚዳረግ ምርቱን ወዲያውኑ ለሚያሰባስቡና ለሚያዘጋጁ ህጋዊ ነጋዴዎች/ወኪሎቻቸው/ ወይም ፋብሪካዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ለፋብሪካዎች በማድረስ አገራችን ከዚህ ምርት የምታገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ለማግኘት እንድትችል በዘርፉ የተሰማሩ አካላትና መላው ህብረተሰብ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪአችንን እናቀርባለን፡፡
ምንጭ፡ ግብርና ሚኒስቴር