መከላከያ ሰራዊት የአይ ኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ፡፡

ሀዋሳ፡ ጷጉሜ 06/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሞኑን የተወሰኑ የአይ ኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ያልተያዙትም በጥብቅ ክትትል ውስጥ መሆናቸውን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ጀነራል ብርሀኑ ጁላ አስታወቁ፡፡ ሰራዊቱ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሀገርና ሕዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ጀነራሉ እንዳስታወቁት፤ አይ ኤስ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለመንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ጥረት አድርጎ ቢመክንበትም በአገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የመለመላቸው፣ ስልጠና የወሰዱና የተጠመቁ ሰዎች እንዳሉ መንግስት በሚገባ እንደሚያውቅ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የአይኤስ አባላት ምን እያደረጉ እንዳሉ፣ የት የት ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ፣ ከእነማን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው፣ በከተሞች ውስጥ ያሉት ሰዎቻቸው እነማን እንደሆኑ፣ ምን እየሰሩ እንዳሉ፣ እቅዳቸው ምን እንደሆነና ሌሎች መግለጽ የማያስፈልጉ ጉዳዮችም እጅግ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው ነው›› ሲል ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል፡፡