የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የቀረቡለትን ጉዳዮች የመለየት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገለጸ፡፡
ሀዋሳ፡ ጷጉሜ 05/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የቀረቡለትን ጉዳዮች የመለየት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም እንደሚገባም አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዶክተር ጣሰው ገብሬ እንደገለጹት፤ አዋጁን መሰረት በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአስተዳደር ወሰን የማንነትና ራስን በራስ ማስተዳደርን አስመልክቶ ጎልተው የወጡ ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ለኮሚሽኑ አቅርቧል።
ከጽህፈት ቤቱ የመጡ ጉዳዮችን በመቀበል ለኮሚሽኑ አባላት መቅረባቸውንና በቀረቡት ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎባቸው ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ተናግረው፤ በኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባር ስር የማይወድቁ ጉዳዮች ተለይተው እንዲመለሱ መደረጉን አመልክተዋል።
 
ክልል ከክልል፣ በክልሎች ውስጥ በሚገኙ ዞኖች እንዲሁም እርስ በርስ በዞኖች መካከል ያሉ ጉዳዮች የቀረቡለት ኮሚሽኑ በዝርዝር እየመረመረ እንደሚገኝ ዶክተር ጣሰው አስረድተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኮሚሽኑ የቀረቡለትን ጉዳዮች በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ያልሰጡት ሰብሳቢው፤ አስፈላጊው ስራ ከተከናወነ በኋላ ጉዳዮቹ ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።