ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጣቸው፡፡
ሀዋሳ፡ ጷጉሜ 05/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአፍሪካ የፖለቲካ አማካሪዎች ማኅበር ሽልማት አበረከተላቸው።
የአፍሪካ የፖለቲካ አማካሪዎች ማኅበር አራተኛ ጉባኤውን “የምርጫ ቅስቀሳ ፋይናንስና ምርጫ በአፍሪካ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኬሂንዳ ባሚግቤታን እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ማሻሻያ አድርገዋል።
በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እስረኞች እንዲፈቱና በውጭ የሚኖሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ወደ አገራቸው በነጻነት እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
 
ወደ አገራቸው ከመጡ በኋላም ከፖለቲከኞቹ ጋር ተቀራርበው መስራታቸውንና ከምሁራን ጋርም የፖለቲካ ምህዳር መፍጠራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ማህበሩ ይህንን ተግባራቸውን ከግምት በማስገባት የአፍሪካ የዓመቱ የዴሞክራሲ ተሸላሚ እንዲሆኑ መወሰኑን ነው የጠቆሙት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመጧቸውን አዎንታዊ ለውጦች ለማስቀጠል መሥራት እንዳለባቸውም የማህበሩ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።
 
ማኅበሩ ከዚህ ቀደም ለሁለት ናይጄሪያዊ ፖለቲከኞች ተመሳሳይ ሽልማት ሰጥቷል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ይህንን ሽልማት ሲቀበሉም ሦስተኛ ግለሰብ ናቸው ብለዋል።
ማህበሩ በአፍሪካ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልውውጥ ልምድ ለማዳበርና በምርጫ ሥርዓት ላይ ያሉ ስልቶችንና ልምዶችን ለመለዋወጥ ይሰራል።
ጎን ለጎንም በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ በአፍሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲዳብር እየሰራ የሚገኝ ማኅበር መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።