የትራፊክ አደጋ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ከ4ሺ 5 መቶ የሚልቁ ዜጎችን ህይወት እንደቀጠፈ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጷጉሜ 01/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2011 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የ4ሺ597 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ እንዳለፈ

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራስያዊ ሪፐብሊክ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገ/እግዚአብሔር ይህን የገለጹት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው “በጷጉሜ ስለ ትራፊክ ደህንነት እንነጋገር” በሚል መሪ ሃሳብ ከጷጉሜን 1 እስከ 3/2011 ዓ/ም ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ አውደ ርዕይ በከፈቱበት ወቅት ነው።

የትራፊክ አደጋው አገሪቱ ካላት አነስተኛ የተሽከርካሪ ቁጥር አኳያ ሲታይ እጅግ የከፋና አሳሳቢ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ሚኒስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል።

የመንገድ አጠቃቀም ህግና ስርአት ባለመከበሩና ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ የመንገድ ትራፊክ አደጋ በአለም ደረጃ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት እያሰከተለ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታዋ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በወጣ የቅርብ ጊዜ መረጃ መሰረት በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚልዮን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ሲያጡ ከ30 እስከ 50 ሚልዮን የሚገመት ህዝብ ደግሞ ቀላልና ከባድ አደጋ ይደርስባቸዋል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየዕለቱ የሚያጋጥሙትን አደጋዎች ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ አዳዲስ ህጎችን የማውጣት፤ አዳዲስ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የማስፋፋት፣ ህጎች የማሻሻል፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ በዘርፉ ውስጥ ድርሻ እንዲኖረው የማድረግ፣ ተቋማዊ አደራጃጀት የማጠናከርና ሌሎች ገንቢ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዲኤታዋ አክለው ገልፀዋል በማለት ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል፡፡