ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተወያዩ፡፡
 
ሀዋሳ፡ ጷግሜ 01/2011 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ዛሬ ጳጉሜን 01 ቀን 2011 ዓ፣ም በቢሯቸው ተወያይተዋል፡፡
 
የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በተደረገው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያለውን አቋምና ያከናወናቸውን ተግባራት አውስተዋል፡፡
 
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የተከናወኑ በጎ ተግባራትን በመዘርዘር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
 
በለውጡ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በውይይቱ የተነሡ ሲሆን በአንዳንድ አካላት እየተፈጸሙ ያሉ ጥፋቶችን በማንሣት ጳጳሳቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም የእርሳቸውም ሆነ የመንግሥታቸው ፍላጎት የተጠናከረች፣ ለሀገር ግንባታ የሚቻላትን ሁሉ የምታደርግና አንድነቷ የተጠበቀ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ማየት መሆኑን ገልጠዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድ መሆን ጥቅሙ ለእምነት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
 
የቀረቡት ችግሮች በለውጥ ውስጥ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሡ ሲሆን ዓይነታቸው ቢለያይም የተለያዩ የእምነት ተቋማት በለውጡ ሂደት ፈተና አጋጥመዋቸዋል፣ በመሆኑም ዕንቅፋት የሚፈጥሩትን አካላት መታገል ያለብን በጋራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
 
የቀረቡትን ችግሮች በዝርዝር በማጥናትና በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር በመነጋገር በጋራ እንደሚፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሀገር ላይ የሚደርሱ ጥፋቶች በሁሉም ላይ የሚደርሱ በመሆናቸው መንግሥትና የእምነት ተቋማት በጋራ በመሥራት መፍታት እንዳለባቸው ገልጠዋል፡፡