“የሚያወጡት እውነት ከሃገራቸው ጥቅም ጋር የሚጋጭ ከሆነ ቅድሚያ ለሃገራቸው ጥቅም ይሰጣሉ” - ዶ/ር ንጉሴ መሸሻ
ሠላም ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን! የዛሬው የንጋት እንግዳችን ዶ/ር ንጉሴ መሸሻ ይባላሉ፡፡ በጋዜጠኝነትና መገናኛ ብዙሃን /በፖለቲካ ኮሚዩኒኬሽን/ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ አሁን ላይ የዋልታ ሚዲያ ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ እና በሃገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ዙሪያ የሚዲያ ሚና ምን መሆን አለበት በሚሉ ሃሳቦች ዙሪያ ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበናል መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡- በቅድሚያ እንግዳ ለመሆን ፍቃደኛ ስለሆኑልን በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢያን ሥም አመሰግናለሁ፡፡
ዶ/ር ንጉሴ፡- እኔም እንግዳችሁ እንድሆን ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- ዶ/ር ንጉሴ ማናቸው? አስተዳደግዎንና የትምህርት ሁኔታ ቢያጫውቱን?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የተወለድኩት በአሁኑ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኝ አርቤጎና በሚባል ከተማ ነው፡፡ አስተዳደጌ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ህፃን ቤተሰቦቼን በማገዝና ትምህርቴን በመከታተል ነው፡፡ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በዚሁ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ግን በሁለት የተለያዩ ከተሞች ነው የተማርኩት፡፡ 9 እና 10 ለኩ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም 11 እና 12ኛ ክፍልን ደግሞ በይርጋዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በ1988 ዓ.ም አጠናቅቄ ወደ ዩኒቨርስቲ አመራሁ፡፡
ንጋት፡- የከፍተኛ ትምህርትዎትን የት ተከታተሉ? ምንስ አጠኑ?
ዶ/ር ንጉሴ፡- በትምህርት ጥሩ ስለነበርኩና ከፍተኛ ውጤት በማምጣቴ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመግባት ዕድል አግኝቼ የውጭ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ በማጥናት በ1992 ዓ.ም ነው የተመረኩት፡፡ ከዛም ለሁለት ዓመት ያህል ካስተማርኩኝ በኋላ በ1995 ዓ.ም አካባቢ ዳግም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በመቀላቀል የሁለተኛ ዲግሪዬን በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ[1]ጽሑፍ አግኝቻለሁ፡፡
ንጋት፡- የሥራ ዓለምን እንዴት ነበር የተቀላቀሉት?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንዳጠናቀኩ ለሁለት ዓመት ያህል በማስተማር ነበር የቆየሁት፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት ስለነበረኝ የሚዲያ ሥራን ሁለተኛ ዲግሪዬ በምማርበት ወቅት ለአንድ ጋዜጣ ከፍተኛ ሪፖርተር በመሆን ነበር የጀመርኩት፡፡ ከዛም ትምህርት እንደጨረስኩ በ1997 ዓ.ም ክረምት ላይ ሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በመቀጠር በ1998 ዓ.ም ሥራ ጀምሬ ከማስተማር እስከ ሴኔት አባልነት ድረስ አገልግያለሁ፡፡
ንጋት፡- የሶስተኛ ዲግሪዎትን (ዶክትሬት ዲግሪ) ስለተማሩበት ሁኔታ ቢያስታውሱን ?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የሶስተኛ ዲግሪዬን የመማር ዕድሉን ያገኘሁት ለዩኒቨርስቲው የመጣውን ነፃ የትምህርት ዕድል /ስኮላርሺፕ/ ተከትሎ ነው። በዚህም ወደ ህንድ በማቅናት በጋዜጠኝነት እና መገናኝ ብዙሃን (journalism and mass communication) የዶክትሬት ዲግሪዬን በ2003 ዓ.ም አጠናቅቄያለሁ፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ያለኝን እውቀት ማሳደግ ስለፈለኩ ሌላ ትምህርት እንድማር ዩኒቨርስቲውን ጠይቄ ስለተፈቀደልኝ ከዶክትሬት ትምህርቴ ጎን ለጎን በፖለቲካ እና ህዝብ አስተዳደር /master of poli[1]tics and public Administration/ ዘርፍ የማስተርስ ዲህሪ መርሃ ግብር በመከታተል ተመርቄያለሁ፡፡
ከዛም ባለፈ በቴያትር ዳይሬክቲንግ ፓስት ዲፕሎማ ተመርቄያለሁ። ከህንድ ቆይታ በኋላም ዳግም ወደ ሃገሬ በመመለስ ባስተማረኝ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት፣ በትምህርት ክፍል ኃላፊነት፣ በኮሌጅ ኃላፊነት እና የዩኒቨርስቲው የሴኔት አባል በመሆን አገልግያለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ነው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመግባት ዕድል ተፈጥሮ በጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ከሁለት ዓመታት በላይ አገልግያለሁ፡፡
ንጋት፡- ወደሚዲያ ኃላፊነት የመጡበት ሂደት እንዴት ተፈጠረ?
ዶ/ር ንጉሴ፡- ቀደም ሲል እንደነገርኩህ አብዛኛው የሥራ ልምዴ እና የተማርኩት የትምህርት መስክ ከሚዲያ ጋር የተያያዘ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምሰራበት ጊዜ ዋልታ ሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ኮርፖሬት እንድመራ የሚያስችል አጋጣሚ ሲፈጠር የበኩሌን አስተዋፅኦ ላበርክት በሚል ወደ ኃላፊነት መጣሁ፡፡ አሁን ላይ የሚዲያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሆንኩ ሦስት ዓመት እያለፈኝ ነው፡፡
ንጋት፡- በሚዲያ ዘርፍ ላይ እንደቆየ ባለሙያ የሃገራችንን ሚዲያ እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የሃገራችንን ሚዲያ በተመለከተ እኔ የፃፍኩት አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አለ፡፡ ጽሑፉ ‹‹ሚዲያ እና ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ/ media and politics in Ethiopia›› የሚል ነው፡፡ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ሚዲያ እና ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ የተሳሰሩ መሆናቸውን የሚያመላክት ውጤት ነው ያገኘሁት፡፡ ይህ በየትኛውም ዓለም ሊሆን ይችላል። ሚዲያው ከፖለቲካው አልያም ከኢኮኖሚ ጋር ሊተሳሰር ይችላል፡፡
የእኛን ሃገር ለየት የሚያደርገው የሚዲያው እና ፖለቲካው ቁርኝት ከፍ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሚዲያውን በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ለራሳቸው ፍላጎትና ዓላማ ማስፈፀሚያ ስለሚያደርጉት ሚዲያው ላይ ያላቸው ተፅዕኖ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሚዲያው የፖለቲካ መጠቀሚያ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ታሪክ ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመነ-መንግስት የመንግስትን ወይም ትዕዛዝ ሰጪ አካል ፍላጎት የሚያራምድ ሚዲያ እንዲሆን ያረገበት ሁኔታ ነበር፡፡
ከዚያም ቀጥሎ በነበረው የኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የሚዲያ አውታሮች በአንፃሩ የተሻሉ ናቸው ተብሎ የሚገመት ሲሆን ወደ 206 የሚጠጉ የህትመት ሚዲያዎች እንደነበሩ የዘርፉ ፀሐፍትና እኔም በጥናቴ ያረጋገጥኩት ነው፡፡ ነገር ግን ወረቀት ላይ ያለው ጦርነት ምድር ላይ ካለው ጦርነት በተለየ ሁኔታ ካምፕ መስርተው እዚህና እዛ ሆነው የመታኮስ(የቃላት ጦርነት) የነበረበት ነው፡፡
ከዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ ውስጥ ሚዲያው የህዝብን ፍላጎት ከማገልገል ይልቅ የፖለቲካ ፍላጎትን የሚያገለግል እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የፖለቲካ ፍላጎት ሲባል በሁለት መልኩ ነው መረዳት ያለብን፡፡ ይህም ማለት በአንድ በኩል መንግስትን የሚደግፉና የመንግስትን እሳቤ የሚያራምድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስትን አልደግፍም ብሎ የሚያስብና የሚቃወም ሆኖ በመንግስት ላይ ጦርነት የሚሰብክበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡
በዚህም የተነሳ ለአንድ ሃገር ሳይሆን ለተለያዩ ሃገራት የሚሰሩ ሚዲያዎች እስኪመስሉ ድረስ የተለያዩ ፍላጎቶች የሚያራምዱ ነበር፡፡ በግል ሚዲያዎች በኩል የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ ከመደገፍ / የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ከመትከል ይልቅ የማፍረስ ሁኔታ ይታይባቸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል ያለው የመንግስት ሚዲያ ደግሞ ሁሉን ነገር በጎ አድርጎ የሚያቀርብና እንከኖችን ደፍሮ ለመዘገብ የማይደፍር እንዲሁም እውነታዎችን የመካድና እንዳላየ ሆኖ የማለፍ ሁኔታ ይታይባቸው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁን በመጣነው የሚዲያ ዕድገት ውስጥ አሁንም ብዙ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም በ1999 የወጣው የብሮድካስት አዋጅ እና በ2000 ዓ.ም የወጣው የሚዲያ ተደራሽነትና ነፃነት አዋጅ ለዕድገቱ ጥሩ ናቸው ብሎ ማንሳት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ሥርዓት ደግሞ የሕዝብ የሪፎርም ጥያቄ የሚነሳበት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በመሆኑ አዲስ የመጣው የለውጥ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አለብኝ ብሎ ‹‹የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2013›› ተብሎ የሚጠራ የሚዲያ አዋጅ እንዲወጣ ጥረት አድርጓል፡፡
በዚህ አዋጅ በሚዲያ ዘርፍ ላይ የነበሩ የሚዲያ ነፃነትን የሚጋፉ ማነቆዎችን ማስወገድ በሚችል መልኩ የመጣ በመሆኑ ጥሩ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ነገር ግን መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በአተገባበር ደረጃ የግሉም ሆነ የመንግስት ሚዲያ አሁንም በሚፈለገው ልክ እየተጓዙ ነው ተብሎ ሊወደስ አይችልም፡፡
ንጋት፡- ሚዲያ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያገናኛቸው ነገር ይኖር ይሆን? አዋጁስ ምን ይላል?
ዶ/ር ንጉሴ፡- ሁለቱ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ጉዳዮች ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ ሲባል ሁለቱም ወደተሻለ ደረጃ የሚደርሱት በሂደት ሲሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለባቸው ሃገራት የሚዲያው ዕድገትም ፈጣን ነው፡፡ ዴሞክራሲ በአንድ ጀንበር ተገንብቶ የሚያልቅ ጉዳይ ባለመሆኑ የሚዲያውም ሥራ ከዴሞክራሲ እሳቤ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡
በመሆኑም የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ሲወድቅ አብሮ የሚወድቅና የሚናጋ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ግን የዴሞክራሲ አውታር አለ ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ዘመን ውስጥ አሁንም የሚታይ ችግር አለ፡፡ በተለይም ከማህበራዊ ሚዲያ መምጣት ጋር ተያይዞ በጣም ፅንፍ የረገጡ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አለ በሚል ሃይማኖትን ከሃይማኖት እና ብሔርን ከብሔር ሊያጋጩ የሚችሉ አስጊና ለኢትዮጵያዊነትም ሆነ ለሃገር አንድነት አስፈሪ የሆኑ ነገሮች ሲዘገቡ እናያለን፡፡
እነዚህ መፍትሄ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች ቢሆኑም እንደ ህግ ግን አዋጁ በአብዛኛው ለግሉ ወይም ነፃ ፕሬስ ለተባለው ዘርፍ የሚወግን ሆኖ ነው የወጣው ማለት ይቻላል፡፡ በአንዳንድ ወገኖች በኩልም መንግስት ነው ጥያቄ ሊያነሳ የሚገባው ሲሉ ይደመጣሉ። ለምሳሌ በቅርቡ እየተነሳ ያለው የሚዲያ ቦርድ ሲቋቋም የመንግስት አካል መወከል የለበትም የሚለው የክርክር ሃሳብ ማሳያ ነው፡፡
ስለዚህ በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ የመንግስት ሚና ምንድን ነው መሆን ያለበት፤ ሚዲያ ነፃ ነው ሲባልስ እስከምን ድረስ ነው የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ካልሆነ በስተቀር አዋጁ ጥሩ ነው፡፡ በመንግስት ሚዲያ በኩል ክፍተቶች አሁንም አሉ፡፡ ለምሳሌ ደፍሮ ያለመዘገብ፣ ጋዜጠኛው ራሱ በፍርሃት ውስጥ መሆንና በተለያዩ ፍላጎቶች ውስጥ በመውደቅ (በብሔር፣ ሃይማኖት ወዘተ) ደፍሮ የመዘገብ ችግር ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል። ከዚህ ውጪ አዋጁ እንደ ህግ የሚገድብ ምንም ነገር የለውም፡፡
ለዚህም ነው ማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ በዩቲዩብ እና በተለያዩ መንገዶች ነፃነታቸውን በመጠቀም ያለገደብ የሚፅፉና የሚናገሩ በርካታ ሰዎች ማየት የተቻለው፡፡ በመንግስት ሚዲያው በኩል ግን ከጋዜጠኛው የግል ተነሳሽነት እና የሚዲያ አመራሩም ተገቢ ካልሆኑ ሥጋቶች በመነጨ ህጉ የሚሰጠውን ነፃነት ያለመጠቀም ሁኔታ አለ ካልተባለ በስተቀር ህጉ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ የምንሰራው ለሃገራችን እና ለህዝቦቿ ጥቅም እስከሆነ ድረስ ኢትዮጵያን የሚጎዳና ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ ከሆነ አንዘግብም፡፡
ይህንን ቢቢሲም ሆነ ሲኤን ኤን የሚያደርገው ነው፡፡ ማንኛውም ሚዲያ ሲቋቋም የሃገሩን አልያም የአህጉሩን ጥቅም የማስከበር ፍላጎትን ተከትሎ በመሆኑ በዛ መርህ ነው መሰራት ያለበት፡፡ ለምሳሌ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ወገንተኝነቱ ለአሜሪካ አልያም ለእንግሊዝ እና ለምዕራቡ ዓለም ጥቅም ነው፡፡ ይህ የፍላጎት ጉዳይ ነው፣ ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ከመሥራት አንፃር የሃገራችንን ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ካገኘን እኛም ባንዘግበው ይሻሻል ብለን የምንተወው ካልሆነ በስተቀር በሚዲያው ዘንድ በአንፃሩ የተሻለ ነገር እንዳለ ማንሳት ይቻላል፡፡
እንደውም አንዳንድ ወገኖች ሚዲያው ነፃ ከመለቀቁ የተነሳ መንግሰት ለምንድን ነው ማህበራዊ ሚዲያውን የማይዘጋው፣ የግል ሚዲያውንስ የማይቆጣጠረው ብሎ ሲተቹ ይሰማል፡፡ ይህ የሚያሳየው የተሰጠውን ነፃነት በተገቢው መንገድ እየተጠቀምን አለመሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ውስጣዊ ምክንያቶች ቢጠቀሱም የውጪ ኃይሎች ፍላጎት አንዱ ገፊ ምክንያት ነው፡፡ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተብለው የሚጠቀሱ ሃገራትና አደጉ የተባሉ ምዕራባዊያን ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የሚከፍቱበት እና ሚዲያውንም ስፖንሰር በማድረግ ጭምር እንደሚሰሩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ንጋት፡- የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ እንደ ህግ የሚያሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ነገር ግን የፕሬስ ነፃነት አሁንሰ አለ ብሎ በድፍረት መናገር እንችላለን?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የፕሬስ ነፃነት አልያም የጋዜጠኞች ነፃነት ሲባል መረዳት ያለብን አንፃራዊ መሆኑን ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ነፃነት የትም የለም፡፡ ጋዜጠኛው ስለሚዘግበው ነገር በእውነታ ላይ ስለመመስረቱ ማረጋገጥ አለበት፡፡ ከዛ ባለፈ የሚያሰራጨውን ዘገባ በተመለከተ ማን ምን አለ? ለምን አለ? መቼና የት ነው ያለው? የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ መቻል አለበት፡፡ ሚዲያዎቹ የሚሰሩት ለሕዝብ በመሆኑ ወገንተኝነታቸው ለእውነት መሆን አለበት። እውነት ስንናገር ለማን ነው የምንናግረው? የሚለው ነው መታወቅ ያለበት፡፡ በሌላ በኩል ሚዲያ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል መንገድ ነው፡፡ መገናኛ መንገድ ከሆነ ደግሞ ህዝብ ምን አለ? የሚለውን መንግስት እንዲሰማ ያደርሳል። መንግስት የሚያስተላልፋቸው የፖሊሲ፣ ዕቅዶችና ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ለህዝብ በሚመጥንና በሚገባ መልኩ ግልፅ አድርገው ያቀርባሉ፡፡
ስለዚህ የሚዲያ ሚና ሁለትዮሽ ነው ሲባል በአንድ በኩል እውነታን መናገር፤ በሌላ በኩል የሕዝብና መንግስት አገናኝ መንገድ ነው ማለት ነው፡፡ እነዚህን መሰረት አድርጎ የሚሄድ ከሆነ ለማንም አይወግንም። ይህ ለመንግስትም ሆነ ለግል ሚዲያዎች የሚሰራ ነው፡፡ እኛ ሃገር የቸገረን እይታችን ስለሆነ ሚዲያዎቹም ጎራ ለይተው የግሎቹ የሆነ ጥግ ይይዙና ሌላውን ለማጥቃትና ለማድማት የመተኮስ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ፡፡
የመንግስት የሚባሉትም ከእነሱ ተቃራኒ ናቸው የሚሏቸውን የመፈረጅ፣ ጫና የማሳደርና ተገቢ ያልሆነ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶችን የመፈፀም ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ሚዲያ የሚሰራው ለህዝብ ጥቅም እስከሆነ ድረስ ከህዝብ ፍላጐት ውጪ የሆነ ነገር ሲያጋጥም አቋም ይዞ የሚሰራ መሆን አለበት፡፡ ይህን በማድረጉ ወገንተኛ ሊያስብለው አይችልምና ለእውነት ወግኖ የህዝብ ጥቅም እንዲከበር መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
ንጋት፡- ዘርፉ ላይ ጥናት እንደማድረግዎ እና ብዙ እንደመሥራትዎ እንደ ጥንካሬ የሚነሱትን ለማስቀጠል እና ድክመቶችን ለመቅረፍ ምን መሥራት አለበት ይላሉ?
ዶ/ር ንጉሴ፡- እንደ ህግ የወጡ አዋጆች ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም አብዛኛው የአዋጁ ክፍል ጠቃሚ ነገሮችን በመያዙ መጠናከርና በተገቢው መተግበር አለበት። ነገር ግን መካተት የነበረባቸውና የተዘነጉ ጉዳዮች ስላሉ ወደፊት ጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍትሄው መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ለምሳሌ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን መሠረት አድርጐ የሚተላለፉ መልዕክቶች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ወሰኑ የቱ ጋር ነው? ማህበራዊ ሚዲያ በዚህ ህግስ እንዴት ነው የሚታዘዘው? የሚለውን ትቶታል፡፡ አንድ ሰው ማህበራዊ ሚዲያውን ተጠቅሞ በህዝቦች አልያም በሃይማኖቶች መካከል ግጭት ቢቀሰቅስ እንዴት ነው ሊጠየቅ የሚችለው የሚለውን በግልፅ አያስቀምጥም፡፡ ከዛ ባለፈ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ቦርድ አባል መሆን አይችሉም የሚለውን ከማንሳት ውጪ ከመንግስት አካል ማን መወከል እንዳለበትም በግልፅ አያስቀምጥም፡፡
የትኛው የፓለቲካ ፓርቲ? ሥልጣን ላይ ያለስ እንዴት አድርጐ ነው ህጉን የሚያስፈፅመው የሚለውን ጥያቄ አይመልስም፡፡ በዚህም ምክንያት ህጉን ድጋሚ ማየት ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ አለኝ። በሌላ በኩል ሃገራዊ የምክክርና ውይይት መድረክ በሚኖርበት ጊዜ የሚዲያዎች ሚና ምን መሆን አለበት? እስከምንስ መሄድ ይችላሉ? በሚል አርቆ ያላየና ያላካተተ ነው፡፡
ንጋት፡- አንድ የፓለቲካ ፓርቲ ሚዲያ አቋቁሞ ባለቤት መሆን ይችላል? የውጪ ሃገራት ልምድ በዚህ ዙሪያ ምን ያሳያል?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የሃገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የፓለቲካ ፓርቲ ልሳን ሊኖረው ይችላል፡፡ በኘሬስ/በህትመት ሊሆን ይችላል በሌላም፡፡ ነገር ግን ተደራሸነታቸዉ የተወሰነ እና ለሚፈልጉት ተከታያቸው ብቻ ነው፡፡ በሌላው ዓለም በየቀኑ የሚወጡ/የሚታተሙ የህትመት ውጤቶች በርካታ ናቸው፡፡ ለምሣሌ በአሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በህንድ ከ5ዐዐ የሚበልጡ በየቀኑ የሚወጡ የህትመት ውጤቶች አሉ፡፡ ብዙ አማራጮች በመኖራቸው የአንተን ድምፅ የሚወከሉትን ጨምሮ የተለያዩ ሃሳቦች ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን ጐልተው የሚሰሙት የተመረጡ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በእኛ ሃገር ለምሣሌ ከህትመት ውጤቶች ተነባቢ ናቸው የሚባሉት የኮፒ መጠናቸው ትንሽ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት የመንግስት ፓሊሲ እስከመቀየር የሚደርስ ተፅዕኖ የማሳደር አቅማቸው እንደ ኮፒ መጠናቸው ጥቂት ነው፡፡ ወደ ብሮድካስት ሚዲያው ስትመጣም የቴሌቪዥን ዘርፍ በተለይ የግሉ የአራት ወይም አምስት ዓመት ታሪክ ነው ያላቸው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ክልሎች የየራሳቸውን ሚዲያ በማቋቋም ባለቤት ሆነዋል፡፡ የተቋቋሙትም የፓለቲካ ሥርዓቱን ተከትሎ በመሆኑ በየክልሎቻቸው ታጥረዋል። ስለዚህ የየክልላቸው ዋስና ጠበቃ የመሆን ዝንባሌዎች ይታይባቸዋል፡፡
በዚህ የተነሳ የቃላት ጦርነት የሚካሄድባቸው ሜዳ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የባለቤትነት ሥርዓቱ ከፓለቲካ ሥርዓቱ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ ባለቤትነት በተመለተ ህጉ በግልፅ እንዳስቀመጠው አይፈቀድም፡፡ በዚህም ፓርቲዎች የቴሌቪዥን አልያም የሬዲዮ ጣቢያ ከፍተው በመምራት ለቃላት ጦርነት መጫወቻ ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ነገር ግን ሃሳቡ ሳይነሳ ወይም ጠቃሜ ሳይሆን ቀርቶ ሳይሆን ሚዲያው ለህዝብ ጥቅም እንጂ የተወሰነ ቡድን ፍላጐት ማስፈፀሚያና መጠቀሚያ እንዳይሆን ታስቦ ይመስለኛል፡፡
በዚህም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታየው ብሽሽቅ የሚመስል ሁኔታ ወደ ህዝቡ በሌላ መንገድ እንዳይደርስ አድርጓል፡፡
ንጋት፡- ጠንካራ ሃገረ- መንግስት በመገንባት ሂደት ውስጥ የሚዲያዎች ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ዶ/ር ንጉሴ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 3ዐ ዓመታት ገደማ በተተገበሩ የተሳሳተ እሳቤ ብሔር እና ህዝብ የሚሉ ነገሮች በተሳሳተ መንገድ ተተርጐመዋል የሚል እምነት አለኝ። ብሔር ማለት በግፅዝ ህዝብ አልያም ሃገር ማለት ሲሆን የጋራ ማንነት ያለው ማህበረሰብ ማለት ነው፡፡ እንደ ሃገር በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተለያየ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ ነው። ስለዚህ ጠንካራ-ሃገረ መንግስት እንገንባ ስንል የትኛው መንግስት (የክልል ወይስ የኢትዮጵያ) በሚል ጥያቄ እየተነሳ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጐት ቆይቷል፡፡
ስለዚህ በአንድ ሃገር ውስጥ የተለያዩ ነፃ መንግስታት በሚመስል መልኩ የተቋቋሙበትን መንገድ በማስተካከል ጠንካራ ሃገረ-መንግስት ለመገንባት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዚህ በፊት የነበሩ ትርክቶችን ተከትሎ ማዕከላዊ መንግስቱ ደካማ እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፍረስ ታቅዶ የተሰራ ይመስላላ የሚል ጥያቄ እንድታነሳ ያስገድዳል፡፡ አንድ ክልል ለሌላው አስፈላጊ መሆኑን ካላወቀና በጋራ ጠንካራ ሃገር መመስረት ካልቻለ በምንም ሊግባቡ አይችሉም፡፡
ይህ በመሆኑም ባለፉት 3ዐ ዓመታት በተዘራው ሴራ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄና ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀ ነበር፡፡ በዚህም ለሚነሱ አንድ ጠንካራ ሃገረ- መንግስት ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ ‹‹ልጨፈለቅ ነው›› የሚል ሥጋት ውስጥ በመግባት ከመተባበር ይልቅ መጠራጠር ይታይ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሙ አስቃቂ ሁነቶች ተከስተው ወንድም በወንድሙ ላይ በመነሳት የሚጠፋፋው። ይህም ጠንካራ ሃገረ-መንግስት የመገንባት ሂደቱን በመፈተን አስቸጋሪ ያደረገው፡፡ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ለምንድን ነው ይህ ሁሉ ሴራ የሚሰራብን? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ለመፍትሄው መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ተጠቃሽ ከሥልጣን የተገፋው አካል/ወያኔ ጥቂት ሆነው ብዙሃንን አሁንም የመምራት ፍላጐት ለማሳካት መንቀሳቀሳቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ፍላጐት መጠቀም የሚፈልጉ የውጪ ኃይሎች መኖራቸውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የተከፋፈለችና የተዳከመች ኢትዮጵያ በመፍጠር በመጨረሻ እንድትፈርስ የሚሰሩ መሆናቸውን ማወቅና ፍላጎታቸው እንዳይሳካ መትጋት ከዜጐች ይጠበቃል፡፡
ከዚሁ ጋር አብሮ የሚነሳው ከዓለም የወደፊት ፖለቲካ ከውሃ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ከወዲሁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ከመገንባት ባለፈ በቀጠናው ካላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጋር ተደምሮ ጠንካራ ሃገር እንዳትሆን እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ዓቀፍ የፓለቲካ ሚዛን ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ የሪዮተ-ዓለም ፍላጐታቸው ለመጫን የሚደረግ ፉክክር ጠንካራ ሃገረ-መንግስት የመመስረት ሂደቱ እንዳይሳካ የማድረግ እንቅስቃሴ አለ፡፡
ይህን ፍላጐታቸውን ለማሳካት ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የሚዲያ አውታሮች በገንዘብ አልያም በሃሳብ በመደገፍ ሂደቱ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ እየተረባረቡ ነው፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ሃገረ መንግስት እንዲፈጠር ውጫዊና ውስጣዊ ኃይሎች በቅንጅት እንደሚሰሩ በመረዳት ህዝቡ ይህን መቀልበስ የሚያስችል መረዳት ላይ እንዲደርስ ሚዲያው አቅዶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
ንጋት፡- የሃገር ጥቅም እንዲከበር እና ጠንካራ ሃገረ-መንግስት የመገንባት ሂደቱ እንዲሳካ ከሚዲያ አመራሮች፣ ከጋዜጠኛውና ከህብረተሰቡ ምን ይጠበቃል?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የሃገርን ብሔራዊ ጥቅም በተመለከተ የሚነገሩ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ ማድረግና በማስተዋል መሥራት ያስፈልጋል። አንድ ጋዜጠኛ ሥራውን ሲሰራ ነፃ ሆኖ ነው፡፡ ነገር ግን ነፃነቴ እስከምን ድረስ ነው የሚለውን ማወቅና መረዳት አለበት፡፡ ነፃነቴ ከኢትዮጵያዊነቴን ከበለጠና ኢትዮጵያዊነቴ አደጋ ውስጥ የሚከት ከሆነ የት ሆኜ ነው ሥራዬን የምሰራው? የትስ ሆኜ ነው ጋዜጠኛ የምሆነው? የሚለውን መመለስ አለበት፡፡ ቅድም እንዳልኩት ጋዜጠኞች እውነትን ወግነው መሥራት አለባቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን የሚያወጡት እውነት ከሃገራቸው ጥቅም ጋር የሚጋጭ ከሆነ ቅድሚያ ለሃገራቸው ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡
ይህ ሲባል ግን ሌላው ዓለም ይጐዳ ማለት አይደለም። ለምሣሌ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሁላችንም ጋዜጠኞች እንደዜጋው አንድ ዓይነት አቋም ነው የያዝነው፡፡ ለምን ከተባለ የሃገር ብሔራዊ ጥቅም ስለሆነ ነው መልሱ፡፡
ነገር ግን የመንግስትን አሰራር፣ ፓሊሲና አፈፃፀም ምክንያታዊ በሆነ በመረጃ አስደግፈን መተቸት አለብን፡፡ ትችታችን ለሆነ አካል ስንል አልያም ለሆነ ጥቅም ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም መከበር እውነት ላይ ቆመን መሆን አለበት፡፡ የሚዲያ አመራሮችም ጋዜጠኞቻቸው እውነትን መሠረት አድርገው በመረጃ የተደገፈ ሥራ ሲሰሩ ከመከልከል ይልቅ በማገዝ የህዝብ ጥቅም እንዲከበር ሊሰሩ ይገባል፡፡ የጋዜጠኝነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ህጉን ጠብቀው ለእውነት ወግነው ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው፡፡
ንጋት፡- በመጨረሻም መቅረብ የለበትም የሚሉት መልዕክተ ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?
ዶ/ር ንጉሴ፡- የምንሰራው ለሃገር ነው። ሃገር ደግሞ የምትቀጥለው በትውልድ ነውና ትውልድን ከግምት ያስገባ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ሃገር ማለት ሰው እና ግዛት/ድንበር ነው የሚል አቋም አለኝ። የሰው ልጅ ድንበር ባይኖረው ሃገር ሆነው መንግስትን መመስረት አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሆነ ስለ አህጉራችንና ዓለማችን ለማሰብ ሃገር ሆነን መቀጠል አለብን፡፡
ይህንን ለማስጠበቅ ደግሞ አንድነታችንን በማጠናከር ለሉዓላዊነታችን መታገል አለብን፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ለእኛ መኖር ብርታታችን የሃገር መኖር በመሆኑ ለህልውናችን ስንል ጭምር ሃገራችንን ማስቀጠል ይጠበቅብናል፡፡ ሁለተኛ በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረግብን ዘመቻ መንስኤ በመረዳት ፍላጐታቸው እንዳይሳካ በጋራ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ሃገራችን ወደቀደመ ገናናነቷና ክብሯ በመመለስ ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ሃገር የመፍጠር ሂደት ቀላል ይሆናል እና ለተግባራዊነቱ እንትጋ እላለሁ፡፡
ንጋት፡- ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በድጋሚ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ፡፡
ዶ/ር ንጉሴ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ። በርቱ፡፡
በካሡ ብርሃኑ