“ለባላንጣዎቿ ትምህርት የሰጠች ሀገር”
ከወደ ሰሜን አትላንቲክ፣ የምድራችን ልዕለ ኃያሏ ሀገር አሜሪካ በየቀኑ ማለት በሚያስችል መልኩ የንጹሃን ዜጎቿ ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ እየተቀጠፈ ነው፡፡ በዓመት እስከ 45 ሺህ ዜጎቿን ሕገወጥ መሳሪያ በታጠቁ ሰዎች በሚፈጸም ግድያ የምታጣው ሀገሪቱ፣ የመሳሪያ ቁጥጥር ላይ ጠበቅ ያለ ሕግ ለማውጣት ጥድፊያ ላይ ብትገኝም የዜጎቿ የመኖር ዋስትና ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ግን የጆ ባይደንን መንግስት እያስተቸ ነው፡፡ ይህም የአሜሪካ የወቅቱ ራስ ምታት ሆኗል፡፡
ላቲን አሜሪካዊያኑ ደግሞ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ድቀት ውስጥ የገባውን የምጣኔ ሃብት ለማስታመም ጥረት በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት፣ የዋጋ ግሽበት ከተጠበቀው በላይ በማሻቀቡ ድህነት ደጋግሞ በራቸውን እያንኳኳ ነው፡፡ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥም ፍዳ ሆኖባቸዋል፡፡ አህጉራችንም አፍሪካ ከዚሁ የዘለለ ገጽታ የላትም፡፡
በአብዛኛዎቹ ሀገራት የፖለቲካ ቁርሾ በመንሰራፋቱ ምክንያት የዜጎች ዕጣ ፈንታ ወደ ባህር ማዶ መሰደድ ከሆነ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ድርቅ፣ ረሃብ፣ የኑሮ ውድነት እና ድህነት ዛሬም አህጉሪቱን እያሽመደመዷት ነው፤ ምንም እንኴን የዚያኑ ያህል የኢኮኖሚ እድገት ቢኖርም፡፡ ከወደ መካከለኛውና ሩስ ምስራቅ ዛሬም ሁለት ጉራማይሌ መልኮች መንጸባረቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ብልጽግና እና ድህነት፤ ወይም ደግሞ የተረጋጋ ፖለቲካ እና ግጭት በየፈርጃቸው ሀገራት እየተናጡበት ያለው ጉዳይ ነው፡፡
ለማንኛውም ዓለማችን ዛሬ ላይ ከየአቅጣጫው የተለያዩ ሁነቶችን እያስተናገደች ነው፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ በለጸጉ የተባሉት ሀገራትም የሚደቆሱባቸው ነገሮች አይጠፉም፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዋጋ ግሽበትና የፖለቲካ ልዩነቶች በእነርሱም ዘንድ መስተዋሉ አልቀረም፡፡ በፖለቲካውም ሆነ በምጣኔ ሃብት ከየትኛውም በላይ የወቅቱ ርዕስ የሆነችው ደግሞ ሀገረ ሩስያ ናት፡፡
ሩስያ በአንድም በሌላ መልኩ አሁን ዓለም ለገጠማት መከራ ተጠያቂ ተደርጋለች፣ በምዕራባዊያኑ ምልከታ፡፡ በቆፍጣና መሪዋ ቭላድሚር ፑቲን እየተመራች የአሜሪካና ምዕራባዊያኑን ውንጀላ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በአቋሟ ፀንታ ያመነችውን ከማድረግ ወደ ኋላ አላለችም። በአሜሪካ እና ኔቶ አለሁልሽ ባይነት ወደ ጦርነት የገባችው ዩክሬንም ከሩስያ የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመከት አቅም ያጣች ትመስላለች፡፡
ይህ ደግሞ የሩስያ ባላንጣ የሆኑት እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ ያሉትን ሀገራት ያስደሰተ አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ ዩክሬን ከሩስያ ጋር ጦርነት ውስጥ እንድትገባ የገፋፏት ሞስኮን ለባላንጣዎቿ ትምህርት የሰጠች ሀገር በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ለማሽመድመድ ብዙ ወጥነው ነበር፡፡ ዩክሬን ከአሜሪካና አውሮፓዊያኑ ጋር የውትድርና ሕብረት ፈጥራ እንዳታዳክማት ሩስያ ስጋት አላት በሚል ሰበብ ምዕራባዊያኑ የሞስኮን ፖለቲካ ለመምታት ቀዳዳዎችን ሲፈልጉም ነበር፡፡ በተለይም በአውሮፓዊያኑ 2014 ሩስያ በደቡባዊ ዩክሬን የምትገኘው ክሬሚያ ወደ ራሷ ግዛት እንድትጠቀለል ካደረገች በኋላ ከአሜሪካ እና ከምዕራባዊያኑ ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ፖለቲካዊ ቁርሾው እየተካረረ መጥቷል፡፡
ሩስያ እና ዩክሬን በጋራ መተዳደር ከጀመሩ ከ1 ሺህ 300 ዓመታት በላይ ታሪክ ሲኖራቸው በየዘመናቱ በጠንካራ መንግስታት እና በሕብረት ደረጃ አብረው ሲተዳደሩም ነበሩ፡፡ የሶቭየት ሕብረት ሲመሰረት አንዳንድ ዩክሬናዊያን በሕብረቱ ስር መሆናቸውን ባይደግፉም ዩክሬን አካል ሆና መቀጠል ቻለች፡፡ ሕብረቱ ከፈረሰ ከ1991 በኋላ ግን የሁለቱ ሀገራት ልዩነት እየሰፋ መጥቶ ዛሬ ላይ ወደ ጦርነት አምርቷል፡፡ አውሮፓ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ አስተናግዳ የማታውቀውን ጦርነትም ለማስተናገድ ተገዳለች፡፡ በየካቲት ወር 2022 ፕሬዝደንት ፑቲን ሩስያዊያንና ዩክሬናዊያን ወንድማማቾችና አንድ ሕዝቦች እንደሆኑ፣ ሩስያ ደግሞ ታላቅ ወንድም ስለመሆኗ ገልጸው ነበር፡፡ ይህም በዩክሬናዊያን ዘንድ አልተወደደም፡፡ “ሩስያ የዩክሬንን ነጻነት አትቀበልም፤ ሙሉ ለሙሉ ማስተዳደር ትፈልጋለች” በሚል የዜለንስኪ መንግስት ራሱን ከማንኛውም ጥቃት እንደሚመክት አስታወቀ፡፡
ይህንን አጋጣሚ የተጠቀሙት ምዕራባዊያኑም ሞስኮ ኪዬቭን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ትፈልጋለች በሚል የሁለቱ ሀገራት ውጥረት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲቀየር ሲያራግቡ ቆዩ፡፡ “ዩክሬን የኔቶ አባል መሆን ትፈልጋለች፤ ይህም ፍላጎቷ ሊከበር ይገባል” ሲሉም ሳይወድ በግዱ የፑቲንን መንግስት ወረራ እንዲያካሂድ ጉትጎታ አደረጉ፡፡ አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነትም በምዕራባዊያኑ አጋፋሪነት እውን ሆነ፡፡ ሩስያ በመጀመሪያ ኪዬቭን ለመቆጣጠር ወታደራዊ ኃይሏን አሰማራች፡፡ ሰሜናዊውንና ምስራቃዊውን የዩክሬን ክፍል በመያዝ ወደ ፊት ብትገሰግስም ኪዬቭን አልተቆጣጠረችም፡፡ ይሄኔ አሜሪካና ምዕራባዊያኑ ከውጭ ተመልካች ሆነው በሩስያ ላይ ከመዛት ባለፈ ጦርነቱን የሚያስቆም መላ መዘየድ አልቻሉም፡፡ አንዴ በኢኮኖሚ ማዕቀብ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ማስፈራሪያ መጠቀም ለእነርሱ ትልቁ መሳሪያቸው ነበር፡፡ የጦርነቱን ገፈት የቀመሰችው ግን በዜለንስኪ ስሜታዊና ሁኔታውን ያላገናዘቡ ውሳኔዎች ጦርነቱን ያፋፋመችው ዩክሬን ናት።
ዩክሬን ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ፈረንጆቹ ሰኔ ወር መጀመሪያ ድረስ የ4 ሺህ 395 ንጹሃን ዜጎች ሕይወት እንዳጣችና 5 ሺህ 390 የሚሆኑት እንደቆሰሉ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከወደ ኪዬቭ የወጣ ሌላ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ዩክሬን በቀን ከ100 እስከ 200 ወታደሮችን በሞት ስታጣ፣ 500 የሚሆኑት ይቆስላሉ፡፡ እስካሁን በተካሄደው ጦርነትም ሩስያ የዩክሬንን ሰቨርዶኔስክ፣ ካርኪቭ፣ ዶንባስ፣ ማርዩፑል፣ ሚሊቶፖል እና ኼርሶን ከተሞችና ግዛቶች ተቆጣጥራለች፡፡ የሩሲያ ጥቃት የተጫነባቸው ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ዘግይተውም ቢሆን የጣር ጩኸታቸውን ማሰማት ጀምረዋል። ከሳምንታት በፊት “የሩስያ ወታደሮችን ድምጥማጣቸውን እያጠፋን ነው፤ በዚህም ሀገሪቱ ክፉኛ ተጎድታለች” እያሉ በኩራት ሲናገሩ የተሰሙት ዜለንስኪ፣ አሁን በተገላቢጦሽ የወዳጆቻቸውን ድጋፍ በብርቱ ጠይቀዋል፡፡ ዜለንስኪ ምዕራባዊያኑን ዘመናዊ የጸረ ሚሳኤል መሳሪያዎችን እንዲልኩላቸውም ተማጽነዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ኔቶ እና አሜሪካ ለዩክሬን ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመላክ በጠረጴዛ ዙሪያ ሊቀመጡ ቀነ ቀጠሮ በያዙት መሰረት መክረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የጦርነቱ እርምጃ ከታሰበው በላይ ወደፊት ፈቀቅ ስለማለቱ አስረጂ ነው፡፡ በእርግጥ እነአሜሪካ እና እንግሊዝ አጋፋሪ ቢሆኑም ለዩክሬን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ቀላል አይደለም፡፡ የመሳሪያ አቅርቦት ከማድረግ ጀምሮ ጥቂት ወታደሮቻቸውን በዩክሬን ጎራ በማሰለፍ የእጅ አዙር ፍልሚያ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡(በእርግጥ ጥቂት ወታደሮቿን እንዳሰለፈች የታወቀችው እንግሊዝ ናት) ታዲያ ጦርነቱ በተጧጧፈበት በዚህ ወቅት፣ እንደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሀገራት በየፈርጃቸው እየቆሙ ነው፡፡ የቤቶ አስራ ሁለቱም መስራች አባል ሀገራት ከሩስያ በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉ ናቸው፡፡
ከሰላሳ አባል ሀገራት መካከልም አብዛኛዎቹ ሩስያን የሚቃወመሙ ናቸው፡፡ ከኔቶ ባሻገር አውስትራሊያ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያም የፑቲንን መንግስት ያወገዙና የኢኮኖሚ ማዕቀብ የጣሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ዳሩ ግን የአሜሪካ እና ሌሎች ኃይሎች ግፊት ያልጣማቸው የአውሮፓ ሀገራት አልጠፉም። ከእነዚህ አንዷ የሆነችው ፖላንድ ዜለንስኪ የድረሱልኝ ጥሪያቸውን ለምዕራባዊያኑ ማሰማታቸውን በጽኑ አውግዛለች፡፡ ሩስያ ውጥረት ውስጥ በገባችበት በዚህ ጊዜ፣ ጠላቶች እንደበዙባት ሁሉ አለንልሽ የሚሏት ወዳጆችን አፍርታለች፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሩስያ ድጋፋቸውን እየሰጡ ካሉ ሀገራት መካከል የድንበር አዋሳኟ ቤላሩስ ቀዳሚዋ ነች፡፡ ቤላሩስ የሩስያ ወታደሮች በግዛቷ አልፈው ጥቃት እንዲፈጽሙ የፈቀደች ሀገር ናት፡፡
ኩባ፣ ኒካራጓ፣ ቬኒዙዌላ፣ ኪርጊዝስታን፣ ሶሪያ እና ኢራን የሩስያ ዋነኞቹ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና ሳዉዲ አረቢያ በጦርነቱ ሩስያን ላለማውገዝ እና ገለልተኛ ሆነው ለመቅረብ የወሰኑ ሀገራት መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ታዲያ እነዚሁ የሩስያ ደጋፊ ናቸው ተብለው የተፈረጁት ሀገራት የዲፕሎማሲ በሮቻቸውን ከፍተው በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ አብረው ትሩፋቱን ለመቋደስ እጆቻቸውን የዘረጉ ናቸው፡፡ በሩስያ የማይደራደሩም ናቸው፡፡ ዓለምን በሁለት ተቃራኒ ጎራ እየከፈለ ያለውም ጦርነት አሁንም ቀጥሏል፡፡ ለሩስያ ባላንጣ ለሆኑት ግን እስካሁን ድረስ የተሰማ የምስራች የለም፡፡
ጦርነቱ በሩስያ የበላይነት ተጠናክሮ መቀጠሉ፣ የሞስኮ የምጣኔ ሃብት ይዳከማል ተብሎ ሲጠበቅ እያሻቀበ መምጣቱ፣ የኔቶ ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነሱ በሞስኮ ላይ የተሸረበው ሴራ ስለመክሸፉ ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡ አሁን ዩክሬን ብቻ ሳትሆን አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ኔቶ ውጥናቸው ባለመሳካቱ ሃዘን ላይ ተቀምጠው ከማላዘን ውጪ አማራጭ ያጡ ይመስላሉ፡፡
የአጥማጆችን መረብ በጣጥሶ፣ አፈትልኮ እንደሚወጣ አሳ ምክራቸውን አፍርሳ ዛሬም ኃያልነቷን ያስቀጠለችው ሩስያ፣ ልትበገር እንደማትችል ዳግመኛ ለባላንጣዎቿ ትምህርት እየሰጠች ትገኛለች፡፡ ባላንጣዎቿም ከዚህ ትምህርት ወስደው በጦርነቱ እጃቸውን ይሰጡ ይሆን? ጊዜ ይፈታዋል፡፡
በኢያሱ ታዴዎስ