‘‘መዞር ’’ ና ‘‘መኖር’’
እንዴት ሰነበታችሁ? አለን እኛም ፡፡ ጋሽ ስብሀት ለአብ ‘‘ከመዞር’’ - ይቅርታ ‘‘ከመኖር’’ እላለሁ ብዬ ነው፡፡ እና ‘‘ ከመኖር በላይ ምን አለ?’’ ፣ ይል ነበር፡፡ ኸረ ጋሽ ስብሀት ብዙ ነገር አለ፡፡ ማግባት አለ፤ ልጅ መውለድ አለ፡፡ በዚህ ዓለም ላይ መኖ‘ርህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከመኖር ለማለት ብዬ ከመዞር ስል የቃላት ስህተት ፈፅሜያለሁ አይደል፡፡ የቃላት ነገር ከተነሳ አይቀር፡፡
አንድ ዲግሪ አለኝ የሚል ትልቅ ሰው ነው፡፡ ተቋማዊ አሰራር እላለሁ ብሎ ተቃዋሚ አሰራር ማለቱ አላነሰ ሌላ ደገመኝ፡፡ based አርገን ነው የምንሰራው እላለሁ ብሎ biased አርገን ነው የምንሰራው ብሎ እርፍ፡፡ አንተ ሰውዬ ያንተ ነገር አልለይህ አለኝኮ፡፡ እንደ ‘‘degree ’’ እና ‘‘agree’’ ፍቺው በዝቶ አምታታኝ፡፡
የማግባት ነገር ሲነሳ ሰዎችዬ ይህች ሰሞኑን ራሷን አገባች ተብሎ ስሟ ያ‘ለም ዜና የሆነችው ሰው ነገር እንዴት ነው ? ‘‘የራስ ባል’’ ይሁን አይሁን ‘‘ የራስ- አባል ’’ አላውቅም ፣ ብቻ አንድ ወዳጄ ሴትየዋን እንደዛ ብሏታል፡፡ ነገርየው አነዋዋሪ ነው፡፡ የነውር እና አነዋዋሪ ነገር ከተነሳ አይቀር። ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ካለፈ በኋላ ነው፡፡ እኔና የስምንት ዓመት ልጄ 18ኛው ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ መወዳደሪያ ሠዓት የቴሌቭዥን ስርጭት እስኪከፈት እየጠበቅን ነው፡፡
የዛን ዕለት፣ በዛ ሌሊት ዕንቅልፋችንን ያጣነው እሱም ያጣን በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ‘‘ዘና ዓለም’´ ፣ የሚል ፕሮግራም መታየት ጀመረ፡፡ የፕሮግራሙ መሪ፣ አስተዋቂ ፣ ‘‘HERO’’ የሚለውን የፈረንጅ ሙዚቃ ጋበዘ፡፡ ዘፈኑ ውስጥ መሳም ይሁን መጉረስ የማይለይ ነገር አለበት፡፡ ምን ነካው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ? አስተዋዋቂው ግን እሱን ዘፈን የጋበዘው ‘‘hero’’ መባል ፈልጎ ነው መሰለኝ ፡፡ ምን ‘‘hero’’ ነው ‘‘HE ROW’’ ነውን‘ጂ፡፡ የራሷ ባል ወደ ሆነቸው ሴት እንመለስ።
ድርጊቷ አኗሪ ሳይሆን አነዋዋሪ ነው ተብሎ አልነበር፡፡ ታላቃችን የሚለው ቃል ታለ[1]ኣለቃችን ከሚለው ቃል ፈልቆ የተገኘ ይመስለኛል፡፡ ታለ - አለቃችን የሆነ ሰው ምን ቢል ጠሩ ነው፡- ‘‘ያላገቡ ሴቶችና ወንዶች በሙሉ፣ የራሳቸው ባል፣ የራሳቸው ሚስቶች ናቸው ’’ ነገርየው ያላገቡ አግቡ የሚል አግቦም አለው መሰለኝ፡፡ አግቦው የገባው ወደጃችን ‘‘እኔ ‘የለኝም ፡፡ ያለው ያግባ፡፡
አግብቼ ምን ላበላት ነው’’ አለ ፡፡ ‘‘ያ - ያለው ያግባ የምትለው፤ አንተ የራስህ ሚስት ነህ‘ንዴ?’’ አይለውም! ሳቅ በሳቅ!!! ሰውኮ የተናገረው ነገር በሙሉ በብዙ እየተተረጎመበት አፌን በቆረጠው እያለ ነው፡፡ በነገራችን ስለዜናው ስንነጋገር አንድ ወዳጃችን ሰርጉ ላይ አንድ የሂንዱ ቄስም ተገኝተዋል ብሎ ነበር ፡፡ ‘‘እርሳቸው ሴት ብቻ የተሰበሰበበት ሰርግ ቤት ከተገኙ ምን ቄስ ናቸው፤ ቀሰም ናቸው እን‘ጂ፡፡’’ ለነገሩ የዜናውን ሙሉ ፍሬ ነገር በደንብ ሳያጣራ ነው ሰውየው የተናገረው፡፡ ቄሱ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ‘‘የሂንዱ ሀይማኖት ስለማይፈቅድ አልመጣም አሉ’’፣ ነው የተባለው፡፡
ሳያጣሩ ወሬ ሳይገሉ ‘መላጣ’ ይሉሀል ይሄ ነው፡፡ እኔ የምለው ዓቢይ ይልማ፡፡ ይሄ ሰሞኑን ላይ ብዙ ብዙ ያልተፈቀዱ፣ ከባህላችን ያፈነገጡ አጓጉል ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን አጋልጬበታለሁ ያልከው መፅሐፍ ነገር እንዴት ነው? ሰሞኑን አንድ ቆየት ያለ የሬድዮ ፕሮግራም እያዳመጥኩ ነበር፡፡ ሳዳምጥ ሰዶምና ገሞራ ነበረበት የተባለውን ስፍራ ተመልክቶ የመጣ ሰው ያዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ ሎጥና ሚስቱ ከሰዶምና ገሞራ ሸሽተው እየወጡ ሳለ ፤ የሎጥ ሚስት ወደ ኋላ አትመልከቺ ስትባል ተመልክታ ጨው ሆና ቀረች ይባል የለ፡፡
የሬድዮ ፕሮግራም አዘጋጁ ይኸው አስከዛሬ ጨው መስላ ቆማለች ብሎ ተረከልን፡፡ ኧረ እናንተ ሰዎች በናንተ ዳፋ እኛ አንጥፋ። በጨው ጥፊ ጭው አስደርጋችሁ ጨው አርጋችሁ እንዳታስቀሩን!! ‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ!”
በጌቱ ሻንቆ