የዳርቻ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራ ሳይጀምር ግንባታው እየፈራረሰ መሆኑ በአካባቢው ሕዝብ ላይ ቅሬታ ፈጥሯል
ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የዳርቻ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራ ሳይጀምር ግንባታው እየፈራረሰ መሆኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የእዣ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት በበኩሉ የትምህርት ቤቱ የግንባታ ሁኔታ ህዝቡ ላይ ቅሬታ መፍጠሩን እንደማያውቅና ምላሽም ለመስጠት ዝግጁ አለመሆኑንም ገልጿል።
በሰፍራው አግኝተን ካነጋገርናቸው አካላት መካከል አርሶ አደር ዱላ ሳሊህና አብድልሰመድ ኡመር ይገኙበታል።
ልጆቻቸውን ለማስተማር አስቸጋሪ አካባቢዎች እንዲያልፉ በመገደድ የአራት ሰአት እና ከዚያ በላይ ጉዞ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል ።
ከዚህም የተነሳ ላላስፈላጊ ወጪ ከመዳረግም ባለፈ ተማሪዎች ህይወታቸው ለአደጋ አጋልጠው እንደሚጓዙ አውስተዋል ።
ሌላው አቶ ስዩም ዱላ እና አርሶ አደር ኪዳኔ ወልዴ በአካባቢው የትምህርት ቤት እጦት ለተለያየ ችግር እንዳጋለጣቸው ጠቁመዋል።
ታድያ ከዚህ አስከፊ ችግር ለመላቀቅ የዝግባ ቦቶና የዳርቻ ቀበሌ ነዋሪዎች በመነጋገር በነፃ ሰፊ መሬት ከማመቻቸት ባለፈ ገንዘብ በማዋጣት ትምህርት ቤት ለመገንባት ከ7 አመታት በፊት ጀምረው ወደ ተግባር ገብተው ነበር።
ለዚህም በ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ወጪ አንድ የመማሪያ እና አንድ የአስተዳር ብሎክ ቢገነቡም አገልግሎት ሳይሰጡ ጥገና ተደርጎላቸውም እየፈራረሱ መሆኑን ተናግረዋል ።
አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ አስተዋፅኦ ቢያደርጉም ወደ ስራ ማስገባት ባለመቻሉ ነዋሪዎቹ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል ።
መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ባለማድረጉ እና አመራር ባለመስጠቱም ነዋሪዎቹ ቅሬታ ፈጥሮብናል ብለዋል።
አሁንም መንግስት ከህዝቡ ጎን በመሆን አጋዥ ሊሆን እንደሚገባና ቅሬታቸውን ለማድመጥ ዝግጁ እንዲሆንም ጠይቀዋል ።
በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች እያደረጉት ያለው ድጋፍና ተነሳሽነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
የህዝቡን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የእዣ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ የህብረተሰቡን ቅሬታ እንደማያውቁት በመጠቆም መረጃም ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
ጣቢያችን ቦታው ድረስ በመጓዝ የቃኘውን መረጃ ይዞ ሊያስረዳቸው ቢሞክርም ጉዳዩን በባለቤትነት ለመመልከት ኃላፊው ዝግጁ ሊሆኑ አልቻሉም።
እጅግ ሳቢና ምቹ እንዲሁም ወሳኝ ቦታ ላይ ግንባታው የተጀመረው የዳርቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ስራ ለማስገባት የመንግስት ልዩ ትኩረትን ይሻል።
ዘጋቢ ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ - ከወልቂጤ ጣቢያችን