የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በኬኒያ ናይሮቢ የተደረገው ወታደራዊ ስምምነት ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 15/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በኬኒያ ናይሮቢ የተደረገው ወታደራዊ ስምምነት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።
ዩኒቨርስቲው ነባር ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በአፍረካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በቅርቡ በኬኒያ ናይሮቢ ወታደራዊ ስምምነት መደረጉ የሰላም ስምምነቱን አንድ እርምጃ ወደፊት ያራመደ ተግባር እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከወደሙት መሠረተ ልማቶች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የሰላም ስምምነቱ በመማር ማስተማር ላይ ያለውን አሉታዊ ፋይዳ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዲህ ይገልፃሉ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ያነጋገርናቸው ምሁራን እንደገለፁት የሰላም ስምምነት መደረጉ አስፈላጊና ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ከመሆኑም በላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነቱ በኋላ በኬኒያ ናይሮቢ የተደረገው ወታደራዊ ስምምነት ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ አሁንም ስምምነቱን ዳረ ለማድረስ ቅን ልቦና እንደሚያስፈልግ ምሁራኑ አብራርተዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ በአፍሪካ አደራዳሪነት ውጤት ማስገኘቱ አፍሪካዊያን ችግራቸውን በራሳቸው የመፍታት አቅም ለአለም ማህበረሰብ ያሳየበት መድረክ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጎጂው ህብረተሰቡ መሆኑን ያነሱት ምሁራን የሰላም ስምምነቱ ግብ እንዲመታ መረባረብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ትግራይን ጨምሮ በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎችን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ ለማድረግ ዩኒቨርስቲው ቁርጠኛ መሆኑን የገለፁት የዩኒቨርሲተው ፕሬዘዳንት ፕሮፈሰር ታከለ ታደሰ ሀገር ለመበታተን የተንቀሳቀሱ የውጭ አካለት እንዳልተሳካላቸውም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ድርሻዩ ጋሻው - ከዋካ ጣቢያችን