የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ማካሄድ ጀመረ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዩኒቨርሲው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ1 ሚሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ የፍራፍሬና የደን ችግኞችን ለመትከል ማቀዱንም ገልጿል፡፡
4ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በዩኒቨርስቲው ‹‹አሻራችን ለትውልዳችን›› በሚል መሪ ቃል በይፋ ተጀምሯል ፡፡
የችግኝ ተከላ መረሃ-ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ እንዳሉት ባለፉት 3 ዓመታት ዩኒቨርስቲው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን የሚያጠናክሩ፣ ለምግብነት የሚያገለግሉና ለግቢ ውበት ስራ የሚሆኑ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል በአረንጓዴ አሻራ ስራ ላይ መሳተፉንና ከዚህም ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆነው መጽደቁን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው የ4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በዩኒቨርስቲዉ ስር በሚተዳደሩ የምርምር ማዕከላትና ካምፓሶች ውስጥ 1 ሚሊየን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ በይፋ ተከላ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥም ግማሽ ሚሊየን የሚሆነው ለምግብነት የሚዉሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ለደን ልማት የሚያገለግሉ ሀገር በቀል ዛፎች መሆናቸውንም ዶ/ር ሀብታሙ አክለዋል፡፡
በተለይ በዩኒቨርሲቲዉ ቅጥር ግቢ ዉስጥ በሚገኙ ቢሮዎች አካባቢ እያንዳንዱ ኃላፊ እስከ 1 መቶ ችግኞችን መትከል እንዳለበት በመተማመን ወደ ስራው መግባቱንም አንስተዋል፡፡
ባለፉት 3 ዓመታት ለአካባቢው ማህበረሰብ ከ1 ሚሊየን በላይ ለምግብነት የሚያገለግሉና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ የቡና፣ የአቮካዶና የአፕል ችግኞች መሰራጨቱንና ዘንድሮም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር ሀብታሙ አስረድተዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኪበሞ ዴታሞ በበኩላቸው በዋናው ግቢ ብቻ በተዘጋጀው 6 ነጥብ 5 ሄ/ር መሬት ላይ የአቮካዶ፣ የቡናና የአፕል ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸው ለጽድቀቱም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት በሰጡት አስተያየት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ዓመታት የጊቢውንም ሆነ የአካባቢውን የአየር ሚዛን የሚያስጠብቁና የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ችግኞች መተከላቸውን አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ- ከሆሳዕና ጣቢያችን