የአዲሱ ስርዓት ትምህርት መማሪያ መጽሐፍ እጥረት የመማር ማስተማሩ ሥራ ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት እየሆነ ነው - የሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት መምህራን
ሀዋሳ፡ ሕዳር 15/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአዲሱ ስርዓት ትምህርት መማሪያ መጽሐፍ እጥረት የመማር ማስተማሩ ሥራ ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት እየሆነ እንደሚገኝ በወላይታ ዞን የሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት መምህራን ተናገሩ።
የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት እየተሰራ እንዳለ ጠቁሟል።
በደቡብ ክልል ካሉ ጥቂት የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው በወላይታ ዞን የሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በ1957 ዓ.ም በሱዳን ሚሽን ተቋቁመው በስምንት ተማዎች የመማር ማስተማር ሥራ እንደጀመረ ከት/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ከሀገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምረው የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በዘንድሮም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ተግባሩን እየተወጣ ሲሆን ከትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ናርዶስ አለባቸው እና ተማሪ ትዕግስት ጋልቻ የትምህርት አሰጣጡ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከትምህርት ፍኖተ ካርታ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ የትምህርት ግብአት እጥረት እንዳለ የሚናገሩት የትምህርት ቤቱ መምህራን፤ የትምህርት ግብአት ችግር ተቀርፎ ለተማሪዎች ውጤታማነት የሚያግዙ ተግባራት በመንግስት መከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በመማር ማስተማር ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው የኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት የመምህራን እጥረት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማነስ የተነሳ ትምህርት ቤቱ ከሙሉ አንደኛ ደረጃ ወደ አንደኛ ሳይክል እንዲወርድ መደረጉን የትምህርት ቤቱ ር/መምህር ኑሩ በድሮ ተናግረዋል፡፡
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ የተካተተው የዕይታና ክዋኔ ጥበብ (ፒቪኤ) ትምህርት አዲስ በመሆኑ ማየት ለተሳናቸው ተማሪዎች መጽሐፍት በጊዜ ባለመድረሱ ምክንያት ወደ ኋላ ስለሚቀሩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ባለሙያ አቶ ታዴዎስ ጫንቆ ከመማሪያ መጽሐፍ ህትመት ጋር ተያይዞ ከክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በጥምረት እየተሠራ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ድርሻዩ ጋሻው - ከዋካ ጣቢያችን