የምርምር ውጤቶችና ጥናታዊ ጹሑፎች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 06/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ የምርምር ውጤቶችና ጥናታዊ ጹሑፎች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ለ8ኛ ጊዜ " ምርምር ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት በአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ ተካሂዷል ።
የአርባምንጭ ዩንቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕረዚዳንት ዶክተር አለማየሁ ጩፋሞ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የመማር ማስተማር ሂደት በምርምር የተቃኘ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል ።
የአርባምንጭ ዩንቨርስቲ ከ8 የምርምር ዩንቨርስቲዎች መካከል አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አለማየሁ የምርምር ውጤቶች የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት መፍታት በሚያስችል መልኩ ማከናወን እንደሚገባ አንስተዋል ።
የምርምር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ በተላይ ብቁ የሆነውን የሰዉ ሃይል ለማፍራትና ለምርምር ሥራ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት ዩንቨርስቲው በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል ።
የምርምር ውጤቶች ከጽሑፍ ባለፈ በተግባር ወርደው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከማድረግ አንፃር ክፍተቶች የሚስተዋሉ ቢሆንም አሁን ላይ ጥሩ የሚባል ለውጥ እዬታዬ መምጣቱን የሚናገሩት ደግሞ የአርባምንጭ ዩንቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚዳንት ተባባሪ ፕሮፈሰር በኃይሉ መርዶክዮስ ናቸው ።
ዩንቨርስቲው ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማከናወን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝም ዶክተር በሀይሉ አስገንዝበዋል ።
በዕለቱ ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡት ሙሁራን መካከል ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፓለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር እንዲሁም ተመራማሪና የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ተደራዳሪ ሲሆኑ ከተለያዩ ተቋማት የሚወጡ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመው ውስን በሆነው በሀገር በጀት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ግኝቶች በተግባር ተደግፈው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡና ሥራ ላይ እንዲውል የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሐላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ : ከበደ ካሣዬ ከአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጣቢያችን