የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የፍትሕ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 05/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሕዝብ ጸጥታና ደህንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የፍትሕ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን ዓቃቤ ሕግ መምሪያ ገለጸ።
አቶ ዓለሙ ወሬራ በመምሪያው የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረጽ ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ ሲሆኑ ዜጐች በገዛ ሀገራቸው ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባቸዋል ብለዋል።
ማንኛውም ዜጋ ክብሩና ሰብአዊ መብቱ ተጠብቆለት በሠላም ወጥቶ የመግባት፣ ማህበራዊ ግንኙነቱን የማካሄድና የንግድ እንቅስቃሴዎችን የመፈጸም እንዲሁም ሃሳቡን በነጻነት የማራመድ ሕገመንግሥታዊ መብት እንዳለው በመጠቆም ለሕጉ ተግባራዊነት ሁሉም መተባበር ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።
ባለንበት ወቅት ፖለቲካዊ ለውጡን ተከትሎ ሀገሪቷን ያጋጠማትን የሠላም እጦትና ያለመረጋጋት ችግሮችን ለመቆጣጠር መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ዓለሙ በሕዝብ ጸጥታና ደህንነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የፍትሕ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በግንባር ቀደምነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን የሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ መልክ ያላቸው ግጭቶች ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በመከፋፈል ለዘመናት የነበሩንን የአንድነት፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴታችንን ለመሸርሸር ያለመ በመሆኑ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያነት ነቅተንና ተገንዝበን ለጋራ አንድነት መቆም ይገባናል ሲሉም አክለዋል።
የሕግ የበላይነት ያልተረጋገጠበት ሀገር ለዜጎቹ ምቹ ካለመሆኑም በላይ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ለማራመድ ስለማይቻል በተለይም የሕግ አስከባሪዎች የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በመወጣት ለሕዝብና ለሀገር ያላቸውን አጋርነት ማሳየት ይኖርባቸዋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጌዴኦ ዞን አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት ካላቸው ዞኖች አንዱ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው፣ በሕዝቡ ዘንድ ለሠላም ሥጋት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች በሚስተዋልበት ጊዜ ሕብረተሰቡ ለጸጥታ አስከባሪውና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ጥቆማ በማድረስ የሀገሪቷን ሠላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ይጠበቅበታልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ - ከፍሰሃገነት ጣቢያችን