ዜጎች በሙያቸው በአግባቡና በታማኝነት ሀገራቸውን የማገልገል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 05/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዜጎች በሙያቸው በአግባቡና በታማኝነት በማገልገል የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባቸው ተገለፀ።
"የዜጎች ቀጥተኛ ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በጌዴኦ ዞን ዲላ ፖሊ ተክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የኮሌጁ ምክትል ዲን አቶ አስፋው ከበደ መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት ሠላም፣ አንድነትና መረጋጋት የሠፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባትና የሀገሪቷን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ የእያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ የጎላ ድርሻ አንዳለው አብራርተዋል።
በአሁኑ ጊዜ የተደቀኑብንን ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎችን በጋራ ተቋቁመን እንድናልፍ ሁሉም ዜጋ በየተሠማራበት የሙያ ዘርፍ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ኃላፊነትን በታማኝነት በመወጣት አሰተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ታመነ ገብሬ የደቡብ ክልል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ትምህርት ቢሮ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው።
የዲላ ቴክኒክና ሙያ ፣ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ግርማ ዶሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ታሪካዊትና ሉዓላዊት ሀገር በመሆኗ ጥንትም ያልተፈተነችበት ጊዜ አልነበረም ያሉት አቶ ታመነ ሀገሪቷን ለማሻገርና ወደሚፈለገው የብልጽግናና ዕድገት ጉዞ ለመድረስ የጀግኖች አባቶቻችንን ታሪክ መድገም ይኖርብናልም ብለዋል።
ኦኔግ ሸኔ እና ሕወሓት እርስ በእርሳችን የምንከፋፈልበትና ሀገሪቷ የምትፈርስበትን አጀንዳዎችን በግልፅና በስውር አንግበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም የጠቆሙት ኃላፊው፤ ሀገሪቷ የተጋረጠባትን የመፍረስ አደጋ ለመመከት ታሪካዊ አደራ ተጥሎብናል ሲሉ አሳስበዋል።
በመድረኩ የኮሌጁ አስተዳደር አካላትና ሥራተኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና፣ ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ የመወይይ ሠነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
ዘጋቢ: እስራኤል ብርሃኑ - ከፍሰሃገነት ጣቢያችን