ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከነገለ ቦረና ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታወቀ ።
ኮድ 2 ሰሌዳ ቁጥር A74349 አ.አ እና ኮድ 3 የሰሌዳ ቁጥር B34240 አ.አ የሆኑ የግለሰብ መኪኖች የኮንትሮባንድ ዕቃ ይዘው ከነገለ ቦረና ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ከህብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ ክትትል ተደርጎባቸው ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ሀዋሳ መግቢ ላይ በቁጥጥ ስር መዋላቸውን በጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዴሳ ለማ ገልጸዋል፡፡
መኪኖቹ ከፋብሪካ ስሪት ውጭ በሆነ መልኩ በተሰራላቸው የላሜራ ብይድ ውስጥ የተለያየ ዓይነት ሞባይል ስልኮች፣ የብር ጌጥ፣ የዓይን መነጽር መሥሪያ ግብዓቶች እና ሌሎችም በፍተሻ መገኘታቸውን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ለደሬቴድ ተናግረዋል፡፡
በሁለቱም መኪናዎች ውስጥ የተያዙ የኮንትሮባንድ እቃዎች አጠቃላይ ግምታዊ ዋጋ 8 ሚሊየን 469ሺ 4መቶ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ከ461 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸውን የኮንትሮ ባንድ እንቅስቃሴ በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም አቶ ኢዴሳ ገልጸዋል፡፡ ከህብረተሰብ ጋር በትብብር በተሰራ ሥራ የተገኘ ውጤት መሆኑንም አክለዋል፡፡
ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች መልካቸውን እየቀየሩ ውስብስብ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ በሲዳማ ልዩ ኃይል 1ኛ ቪ.አይ.ፒ ሻሌቃ 3ኛ ሻምበል አዛዥ ዋና ሳጅን ከበደ አለማየሁ ናቸው፡፡ በተለይም ኮንትሮባንድ ይዘው ለማምለጥ የሚሞክሩ ተሸከርካሪዎች የታመመ ሰው ይዘናል፣ እንቸኩላለን የሚሉና ሌሎችንም ምክንያቶች ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ላደረገው ትብብር ያመሰገኑት ዋና ሳጅን ከበደ በቀጣይም ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ