ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ6.3 ሚሊዮን በላይ የደን ችግኞችን በ4ተኛዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመትከል ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው ወደ ተግባር መገባቱን በቤንች ሸኮ ዞን የሼይ ቤንች ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ ።
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት የተተከሉት ችግኞች ውጤታማ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
በ4ተኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከ6.3 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ኒሳብ ተናግረዋል ።
በዚህም እስካሁን 5.8 ሚሊዮን ጉድጓዶችን በማዘጋጀት 4.3 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸዉን በመግለፅ ቀሪ የችግኝ ተከላዉን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያግዙ የጉድጓድ ዝግጅት እና ችግኞችን ለተከላ ወደ ተዘጋጀው ቦታ የማጓጓዝ ተግባር መከናወኑም ተመላክቷል ።
በዚህ መርሐ-ግብር ከሚተከሉ ችግኞች መካካል አብዛኞቹ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ እና እኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸዉ የቡናና ቅመማ ቅመም ችግኞች መሆናቸዉም ተመላክቷል ።
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዙሮች የተተከሉ ችግኞች በተደረገላቸው ክብካቤና ጥበቃ አድገዉ ተጨባጭ ዉጤት እየታየባቸው መሆኑን የገለፀት አስተዳዳሪው የአካባቢው ሕብረተሰብ ከተከላዉ ጎን ለጎን በደን ክብካቤ የጀመሩት ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በወረዳዉ ደንና አካባቢ ጥበቃ የአየር ንብረት ቁጥጥር ልማት ጽ/ ቤት ኃላፊ ዘማች ኪዳኔ በበኩላቸዉ በአሳታፊ የደን ጥበቃ መርሐ-ግብር ከ2700 በላይ አርሶ አደሮችን በ11 ማህበር በማደራጀት የደን ጥበቃና እንክብካቤ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል ።
በዚህም ከዚህ ቀደም በተከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰዉ ማገገማቸዉንና የወረዳዉ የደን ሽፋንም ከነበረበት 9.6 ሄክታር ወደ 18. 6 ሄክታር ከፍ ማለቱን አስረድተዋል ።
ከእርሻ ማሳ ማስፋፋት እና ህገ-ወጥ የከሰል እና ጣዉላ አምራቾች ጋር ተያይዞ በድንበር አካባቢ በደን ላይ የሚደርሰውን ዉድመት ለመከላከል ከአጎራባች ቀበሌዎች ጋር ቅንጅታዊ ስራ መጀመሩን የገለፁት ደግሞ በወረዳው የደን ልማትና ጥበቃ ዋና የቡድን መሪ አቶ ስንታየሁ አባተ ናቸው፡፡
ያነጋገርናቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ባለፉት ሶስት ዓመታት በማህበር ተደራጅተው ደንን በመጠበቅና በመንከባከብ ተጠቃሚ መሆናቸውን በመግለጽ በቀጣይም የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ ፡ ዩሐንስ አሰፋ - ከሚዛን ጣቢያችን