አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይልና ባህላዊ ዕሴቶቿ አድናቆት እንዳላስገኙላት ሁኔታዎች ይመሰክራሉ። ጊዜ ባለፈና ዕውቀትም እየጎለበተ በመጣ ቁጥር አህጉሪቷ በተቃራኒው በእንቅፋቶች ውስጥ መዘፈቁ ጥርጣሬን ያስነሳል፡፡ ብዙ ጊዜ አፍሪካዊያን የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን በመዋጋት ያገኙት ነጻነት መሠረታዊ የሆኑ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን በበቂ ሁኔታ እንዳላስገኙላቸው ይነገራል፡፡
ቢያስገኙላቸውም እንኳን አንዳንድ ጸሀፊዎች እንዳስቀመጡት “ግጭቶች ሳይፈቱ ወይም በከፊል በተፈቱበት ይቀራሉ” ያሉበት አሳሳቢ ሆኖ ይታያል፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅት በአህጉሪቱ የተለያዩ ግጭቶችና የሠላም መደፍረስ ችግሮች የሚታዩበት ነው፡፡ ኢ-መደበኛና በህገ-ወጥ ደረጃ የታጠቁ ቡድኖች የመንግሥታትን ስልጣን ሲያናውጡና ንጹሀንን ሲገድሉ ማየት የዕለት ተዕለት ትዕይንት ሆኗል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አህጉሪቱ አሁን የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ እንመለከታለን። በአንጻራዊነት የውጭ መንግሥታት ጫና ቀንሶ ዜጎች የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶች ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸው ተስፋ የሚያጭር ነው፡፡
አሁን እየታየ ያለው አዝማሚያ ግን እነዚህ ጣምራ ገጾችን በማጥፋት ሥጋቶችን ደቅኗል፡ በኒጀር ወንዝ ዱካና ሳሄል አካባቢ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ በደቡባዊ ምሥራቅና እንዲሁም በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ እየታየ ያለው ሁኔታ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ጭንቀትንም ይፈጥራል፡፡ በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ አሁን ያንዣበበው ውጥረት ከሌሎች በተለየ በጽንፈኛ ቡድኖች ያለመቆስቆሱ ልዩ ቢያደርገውም የአህጉሪቱ መንግሥታት ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት የነበሩበትን ችግር የሚያስታውስ መሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል። በሀገራት፣ ህዝቦችና በመንግሥታት መካከል እየጎለበተ የመጣውን ትሥሥርና የወንድማማችነት ዕሴትን ያጎድፋል፡፡ የዓለም ዋና ዋና የመገናኛ ብዙሀን ሰሞኑን እንደዘገቡት ከሆነ በዴሞክራቲክ ኮንጎ እና በሩዋንዳ መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት ከሯል፡፡ ብዙ ዜጎችን በማፈናቀል ለስደትና እንግልት ዳርጓል፡፡
ተጎራባች የሆኑት ሩዋንዳና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ላለፉት ረጅም ዓመታት ሠላም አግኝተው ያለማወቃቸው አሁን ደግሞ ግልጽ ወደ ሆነ ጦርነት ለመግባት መፋጠጣቸው የዓለም ማህበረሰብና የአፍሪካ ሀብረትን አሳሰቧል። የአፍሪካ ህዝቦችና መንግሥታት እርስ በርስ ለገቡት ቃል ኪዳንም እንቅፋት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በችግሩ ዙሪያ የሩዋንዳ መንግሥት ዴሞክራቲክ ኮንጎን ሲወነጅል፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በበኩሏ ሩዋንዳን መውቀሷ ሀገራት ምን ያህል ሽኩቻ ውስጥ እንደገቡ ያሳያል፡፡ አንዱ ለሌላው በሩን በመዝጋት ምን ያህል የሥውር ጥቃት እየፈጸመ እንደሆነም ያመለክታል፡፡
ሂደቱን በጥልቀት የሚያውቁት መገንዘብ እንደሚችሉት ኤም 23 የተባለው የሩዋንዳ በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ ለምን ውጥረት ነገሰ? አማጺ ቡድን ከሀገሩ ወጥቶ ወደ ኮንጎ ከገባ ወደ 30 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኮንጎ ዜጋ በመምሰል በሀገሪቱ መንግሥታዊ ሥርዓት እየተሳተፈ በሌላ በኩል የሩዋንዳ ታማኝነቱንም ሳያቋርጥ በሁለት ቢላዋ የሚቆርጥ ወዳጅ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ችግሩን በዝርዝር ከዘገቡ ዓለም- አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን መካከል የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ (ዶች ቬለ) አንዱ ሲሆን በተለይ የአማጺ ቡድኑ ወረራን በመቃወም የዴሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎች የሰጡትን አስተያየት አካቷል፡፡ ጥያቄ የቀረበላቸው አብዛኞቹ ዜጎች በተከሰተው ችግር የተቆጡ ሲሆን ለሀገራቸው ነጻነት መስዋዕት ለመሆንም ቃል ገብተዋል። ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን በደልና ሰቆቃ በማስመልከት የሩዋንዳን አምባሳደር ከሀገራቸው ለቆ እንዲወጣ ጥያቄ አቅርበዋል። መንግሥትም የኮንጎ አየር መንገድ ወደ ሩዋንዳ እንዳይበር ከልክለዋል፡፡ የግጭቱ መነሻ ምክንያትና ሊወሰዱ ስለሚገቡ የፍትህ አቅጣጫዎች አስተያየቱን ያሰፈረው ደግሞ የዓለም አቀፍ ቀውስ አስወጋጅ ቡድን የተባለ ድርጅት ሲሆን በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ መንስኤዎችን ጠቅሷል፡፡
ለግጭቱ ዋነኛ መንስኤ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. በ1994 በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ በርካታ የድርጊቱ ተካፋዮችና የሁቱ ጎሳ አባላት ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በመኮብለል ኑሯቸውን አዚያው ማድረጋቸው አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል፡፡ ቀድሞውንም በሠላም ወደ አካባቢው ያልገቡ የቡድኑ አባላት ትንኮሳቸውን ቀጥለው አስካሁን የዘለቁ ሲሆን አልፎ አልፎ በሚያደርጉት ሠላማዊ የፖለቲካ ውይይት ከመንግሥት ጋር ተደራድረው ወደ ሀገሪቱ ጦር መቀላቀልም ችለዋል፡፡ አሁን ዴሞክራቲክ ኮንጎን እየመሩ የሚገኙት ፕሬዝዳንትና የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፈሊክስ ጽሸከዲ ሥልጣን በያዙበት ጊዜ ከቡድኑ ጋር መልካም ግንኙነት መጀመራቸውም ተገልጿል፡፡
በእንዲህ ገባ ወጣ ሲል የነበረው ግንኙነታቸው ግን መቀጠል አልቻለም፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር ተዳምረው ለቀውሱ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እንደ ተንታኞች ገለጻ በሀገሪቱ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም፡፡ እንዲሁም ለሙስና መንሰራፋት አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን መንግሥት ማሳካት ያልቻለው የወታደራዊ ተቋም ለውጥም አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል፡፡ አማጺ ቡድኑ ያገኛቸው ወሳኝ ወታደራዊ ድሎችን በመጥቀስ፡፡ አጎራባች የአካባቢው ሀገራት ማለትም ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ዩጋንዳ እና ብሩንዲን ልዩ የሚያደርጋቸው በሦስቱ ሀገራት ድንበር ተሸጋሪ የሆኑ ማህበረሰቦች መኖራቸው ሲሆን ይህ ለመንግሥታት ግንኙነት መጠናከርም ሆነ መሻከር የራሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
በግዛታቸው የሚገኙ ብሔረሰቦችን ለመደገፍ የሚያደርጉት ጥረት የሌሎችን ድጋፍ ሲያስገኝላቸው የሚያጋጥማቸው የግንኙነት መሻከር ደግሞ ጥላቻና ያለመተማመንን ያስከትላል፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ ቀውስ አስወጋጅ ቡድን ሥጋት ከሆነ የግንኙነቶች መሻከር በአሁኑ ጊዜ ሌላ አካባቢያዊ ቀወስ ሁሉ ወደ ማስከተል ደረጃ እየሄደ ነው፡፡ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ጽሽከዲ የፈጠሩት ዜዴ ሦስቱ የአካባቢው ሀገራትን ወደ ግጭት እንዳያስገባ ተሰግቷል፡፡
ምክንያቱም ከዩጋንዳና ቡሩንዲ ጋር ስምምነት በመፍጠር በሩዋንዳ ላይ ለማነሳሳት ስለወጠኑ፡፡ የአፍሪካ ህብረት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የገነባውን የወዳጅነት፣ የአንድነትና የወንድማማችነት ዕሴትን በማጉደፍ በአካባቢው ግጭትን እየቀሰቀሰ ያለው ማን ነው ከተባለ ወቀሳው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሰው ድንበር ከገባው የኤም 23 ቡድን ጫንቃ አይወርድም፡፡ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊ ሀገራትም ችግሩን በመረዳት በሩዋንዳ መንግሥት ላይ ማዕቀብ እየጣሉ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የጀብደኝነትና ማን አለብኝነት አስተሳሰብ የተጠናወተው አማጺ ቡድን ለማንም እጅ የሚሰጥ አልሆነም። ቀደም ሲል በኬኒያ የተደረሰውን የሠላም ስምምነት መንግሥት በማፍረስ ጥቃት ፈጽሞብኛል የሚል ስሞታ እያቀረበ ሰሞኑን በከፈተው ተጨማሪ ጥቃት ቡናጋና የተባለች የዴሞክራቲክ ኮንጎ ከተማን በቁጥጥሩ አስገብቷል፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው፡፡ አዎን፡- ኤም 23 የተባለው የአማጺ ቡድን አቋም ድብቅ ነው፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ገብቶ በህገ-ወጥ መንገድ ኑሮውን ስለሚያካሂድ። አሰቀድሞ በርካታ ወንጀሎች በፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖችም ስለሚመራ፡፡
ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሌላ ችግር ድብቅ የሆነው የሩዋንዳ መንግሥት አቋም ነው። ሀገሪቱ በአካባቢው ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ካላቸው ሀገራት ዋነኛዋ ስትሆን በኮንጎ በኩል የሚነሳባትን ስሞታ መቼም ተቀብላ አታውቅም፡፡ ሰሞኑን በሁለቱ ሀገራት ድንበር በተፈጸመ የሮኬት ጥቃት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሁለት ህጻናት ተገድለው አንዷ ክፉኛ መቁሰሏ ሲገለጽ አንድ ትምህርት ቤት መውደሙንም አልጄዚራ ዘግቧል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተቀጣጠለው ውጥረት የአፍሪካዊነት ትብብርና የወንድማማችነት መንፈስን ሁሉ የሚጎዳ ነው። የቅኝ ግዛት ሥርዓት በተገረሰሰ ማግሥት በአፍሪካ የተንሰራፋውን ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነትን ያስታውሳል፡፡ አካባቢው ካለው የማዕድን ሀብት አንጻር በተለያዩ የውጭ ሀገራት ኩባኒያዎች ሲፈጽሙ የቆየውን ምዝበራና የመብት ጥሰት ያስታውሳል፡፡
ከሁሉም በላይ በተለያዩ የአፍሪካ አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለውን የአሽባሪዎች ጥቃትንም ስለሚያበረታታ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል እንላለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአሜሪካ መንግሥት ያቀረቡትን አስቸኳይ የተኩስ አቁም ጥሪዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በፈረኦን ደበበ