ሠላምን የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎችን በጋራ በመከላከል የዜጎችን ሠላም እናስጠብቃለን- አቶ አብርሃም መጫ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሠላምን የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎችን በጋራ በመከላከል የዜጎችን ሠላም ለማስጠበቅና አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንሠራለን ሲሉ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሀም መጫ ተናገሩ፡፡
ዋና አስተዳዳሪው ይህን ያሉት የሀዲያ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ምክር ቤት ጉባኤውን በሆሣዕና ከተማ ባካሄደበት ወቅት ነው።
የምክር ቤቱን ጉባኤ በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የሀዲያ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አረገ ማዴቦ እንደገለፁት የዜጎች ሠላም እንዲረጋገጥና የህግ የበላይነት እንዲከበር የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል::
መምሪያው ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት አባላት ጋር በመቀናጀት በዞኑ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ከግብ እንድደርሱ ለማስቻል እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
በተሰራው ሥራ በሠላም እሴት ግንባታ፣ በመረጃ አስተዳደር፣ የግጭት መንሥኤ ጥናትና አፈታት እንዲሁም በሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ክትትል ሥራዎች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም አቶ አረጋ ተናግረዋል።
ህብረተሰብን በማሳተፍ በተከናወኑ የሠላም ግንባታ ሥራዎችም የማህበረሰብን አቅም በማጎልበት ረገድ የተሻለ አፈፃፀም መታየቱንም ገልጸዋል።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የተውጣጡ ሠላም ወዳድ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በግጭት ቅድመ-ማስጠንቀቂያና በመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በማሳተፍ ልከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን እንዳይከሰቱ የማረግና የፀጥታ ስጋቶችንም የመቀነስ ሥራዎች መሠራታቸውን የመምሪያው ኃላፊ አስታውቀዋል።
በጉባኤው የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የፀጥታው ምክርቤት ሰብሳቢ አቶ አብርሃም መጫ ባስተላለፉት መልዕክት ሠለም የመኖር ዋስትና በመሆኑ ሠላምን የሚያናጉና የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎችን በጋራ በመከላከል የዜጎችን ሠላም ለማስጠበቅና አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል።
ሠላም በሌለበት ሀገር ላይ ማንኛውንም የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ማስፈን የማይቻል ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ጠንካራ የሠላም እሴት ለመገንባት ሁሉም ዜጋ መረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።
የሀገርን ሠላም የማስጠበቅ ኃላፊነት ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ጉዳይ ልሆን አይገባም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ወጣቱን ትውልድ ስለሠላም የማስተማር አደራ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በጉባኤው በ2014 በጀት ዓመት በዞኑ የተከናወኑ የፀጥታ ሥራዎች አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከድንበርና ወሰን እንዲሁም ከአደረጃጀት ጥያቄዎች ጋር በሚያያዙ የፀጥታ ሥጋቶች ዙሪያና መሠል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተው ከባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል መቶ አለቃ ብርሃኑ ወልዴና አቶ አለሙ ካሣ መድረኩ በዚህ ወቅት መዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው በሁሉም አከባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ሥጋቶችን ለመቀነስና ሠላማዊ አከባቢ ለመፍጠር ሀሉም ዜጎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንድችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈጥርላቸው ገልፀዋል::
ዘጋቢ፡ ኤልያስ ኤርሶ- ከሆሳዕና ጣቢያችን