መመላለሱ አድክሞን ነበር
ዝናሽ ሾርቤ ትባላለች፡፡ የተወለደችው በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ ነው፡፡ በሁለት ዓመቷ በጠና ታማ እንደነበር ታስታውሳለች። በወቅቱ ህመሟን ያልተረዱት ወላጆቿ ወደ ህክምና ስፍራ አልወሰዷትም፡፡ በዚህም ምክንያት ህመሟ እየባሰ መጣ፡፡ ጭንቅላቷን በጣም እንዳሚያማት ስትነግራቸው ሀኪም ቤት መውሰድ ግድ ሆነባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሀኪም ቤት ሲያደርሷት ችግሩ ወደ ወገቧ እንደደረሰ ለቤተሰቦቿ ነገሯቸው፡፡
ዝናሽ የፖሊዮ ክትባት በወቅቱ ባለማግኘቷ እንደልብ ለመራመድ ተቸገረች፡፡ በድጋፍ መንቀሳቀስ ግድ ሆነባት፡፡ አሁን ላይ በአለታ ወንዶ ከተማ ከቤተሰቦቿ ጋር ትኖራለች፡፡ ካለባት የመራመድ ችግር ጋር እየታገለች እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምራለች። በቤት ውስጥ እራሷን ለመርዳት የተለያዩ በእጅ የሚሰሩ የጥልፍ ስራዎችን በመስራት ታሳልፋለች፡፡ ሥራው ጥሩ ቢሆንም ለስራው የሚሆኑ ግብአቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወደዱ መምጣታቸው ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገባት ትናገራለች፡፡ ዝናሽ ገና ወጣት ናት፡፡ መስራትም ትችላለች፡፡
የአካል ጉዳተኝነት መስራት አያግድም ባይ ናት፡፡ የልብ መሻቷን የምታሳካበት እድል የተፈጠረው፡፡ በዚህ መሀል ነውበከተማው የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ከሚረዱ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ተገናኘች፡፡ ከነዚህ ድርጅቶች አንዱ ሥልጠና በመስጠትና እቃዎችን በማሟላት ስራ እንዲጀምሩ አደረገ፡፡ መንግስት ተደራጅተው ለሚሰሩ አካል ጉዳተኞች የመስሪያ ቤት ባመቻቸው መሰረት የእድሉ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡
አስር ሆነው ለተደራጁት አካል ጉዳተኞች በተሰጠው የመስሪያ ቦታ ላይ የተለያዩ የእጅ ሥራ፣ የጥልፍና ሌሎች ሥራዎችን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ‹‹እኔም ሆንኩ ከኔ ጋር የሚሰሩ አካል ጉዳተኞች በመስራታችን ተለውጠናል›› የምትለው ዝናሽ ‹‹የራሳችንን ገቢ በማግኘታችን ለቤተሰብ ሸክም ከመሆን ተላቀናል›› ብላለች። ‹‹ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል አይተናል። በመስራታችን ችግራችንን ማቃለል ብቻ ሳይሆን ስለሥራችን ብቻ ስለምናስብ አካል ጉዳተኝነታችንን አናስበውም›› ትላለች፡፡ ‹‹እንደኛ አካል ጉዳተኛ የሆኑ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡
ከቤት ያልወጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ከተደበቁበት በማውጣት እንዲማሩና ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ያስፈልጋል›› ትላለች፡፡ በተለይም በገጠሩ አካባቢ ልዩ ትኩረት ተደርጎ መሰራት አለበት ባይ ናት፡፡ ለዚህም በአካል ጉዳተኝነት ላይ የህብረተሰቡ አመለካከት ገና አልተቀየረም።
ስለዚህ ገጠር አካባቢ ግንዛቤ የመፈጠር ሥራ ትኩረት በመስጠት አካል ጉዳተኞች እንዲማሩ እንዲሁም እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል ስትል ሀሳቧን አጋርተናለች፡፡ ዝናሽ እንደምትለው ‹‹አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወደ ተለያዩ ቢሮዎች ተመላልሰን ለመከታተል እንቸገራለን። በተለይ በጉዳተኝነታቸው ምክንያት እንደልብ መንቀሳቀስ ለማይችሉ ጉዳያቸው በፍጥነት እንዲያልቅ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡
አብዛኛዎቻችን መስሪያ ቤት አካባቢ ቆይተን ጉዳያችንን ለመፈጸም ትዕግስት እናጣለን፡፡ የራሳችንን ችግር መሸከም ስለሚከብደን ቶሎ በመሰልቸት ጉዳዩን ሳናስፈጽም እንተዋለን›› ስትል በቢሮዎች አካባቢ የሚገጥማቸውን እንግልት ትናገራለች፡፡ አብዛኛው አካል ጉዳተኛ የመስራት ፍላጎት አለው የምትለው ዝናሽ ለመስሪያ የሚሆን ቁሳቁስ ያለመሟላት እንቅፋት ሆኗል ትላለች። በተለይ ደግሞ የመስሪያ ቦታ ያለማግኘት ሁኔታ የብዙ አካል ጉዳተኞች ችግር ነው፡፡ እኔም ሆንኩ ከኔ ጋር ተደራጅተው እየሰራን ያለነው ቤት ለማግኘት በጣም ተቸግረን ነበር።
በተወሰኑ ሰዎች ብርታት ነው የተሳካው እንጂ እኛ በራሳችን መመላለሱ አድክሞን ነበር፡፡ በአለታ ወንዶ ከተማ ብዙ አካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ እንደ ዝናሽ እድሉን ያገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ተደራጅተውና ስልጠና ወስደው መስሪያ ቦታ ያላገኙም አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአለታ ወንዶ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሀላፊን አቶ ጉሩሞ ጉጋ አነጋግረን ነበር፡፡ አቶ ጉሩሞ እንደገለጹት በከተማዋ የተለያየ አይነት የአካል ጉዳት ያለባቸው 769 ዜጎች አሉ፡፡ ያሉባቸውን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በቂ ነው ማለት አይቻልም።
ለዚህም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር አካል ጉዳተኞች ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን እኛም ጠይቀን እነሱም ከመንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ባላቸው ትብብር ሁለት ዙር ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መሠረት 53 አካል ጉዳተኞች ሰልጥነው በሁለት ማህበራት ተደራጅተው የልብስ ጥልፍ ስራና ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን የማምረት ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ለመስሪያ የሚሆን ቦታ ለማግኘት ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ከዚህ በኋላም ለሚሰለጥኑ ቦታዎችን ለማመቻቸት እየተሰራ ነው፡፡ በመስሪያ ቦታ ያለውን የኤሌክትሪክ ችግርን ለመፍታትም ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ አሁንም ሰልጥነው መስሪያ ቦታ ያላገኙ ስላሉ ተደራጅተው ቦታ እስኪሰጥ እየጠበቁ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በአሁኑ ወቅት የገንዘብ እጥረት ስላለ ፍላጎታቸውን ለማርካት አማራጮችን በመፈለግ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ ሁኔታዎች ቢመቻቹ አካል ጉዳተኞች ሥራዎችን በመስራት ራሳቸውን ከተረጂነት ማላቀቅ ይችላሉ፡፡
መንግስት እና ሌሎችም ረጂ ድርጅቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ከፈጠሩ መስራት ይችላሉ፡፡ የመስሪያ ቦታዎችና አስቻይ ሁኔታዎች ባይሟሉም እንኳ በራሳቸው ጥረት እየሰሩ ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ለነዚህ ትንሽ ድጋፍ ቢደረግ ከዚህ የበለጠ ሰርተው ራሳቸውንም ሆነ ሀገርን የመለወጥ ችሎታ አላቸው፡፡ እንደ ዝናሽ ሁሉ ሰልጥነው እና የሚሰሩበት ቦታ ተመቻችቶላቸው የሚሰሩ አካል ጉዳተኞች ቁጥራቸው በጣም ትንሽ ቢሆንም ሌሎችም ይህን እድል እንዲያገኙ መንግስትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሊረዷቸው ይገባል፡፡
በደረጀ ጥላሁን